Saturday, February 17, 2018

የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር



"የኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር (ኢደማ)  “የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር” (ኢደማ) የስም ለውጥ ያገኘበት 32ኛ ዓመት  መታሰቢያ




የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር (...) ፋሺስት ኢጣሊያ 1929 .. አዲስ አበባ ከተማ ያደረገውን ጭፍጨፋ 23ኛው ዓመት በሚታሰብበት የካቲት 12 ቀን 1952 .. የሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ በነበረው ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶ ተመሠረተ።

ምሥረታ እና አመራር


... በእውቅ ሰዎች እና ደራስያን ሲመራ እና ሲስተዳደር ቆይቷል። ማኅበሩን ካቋቋሙት ደራስያን መካከልም ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ (የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት) ጸሐፌ ተውኔት መንግስቱ ለማ አቤ ጉበኛ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን ለማ ፈይሳ ከበደ ሚካኤል ጳውሎስ ኞኞ የመሳሰሉት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ቀዳሚ የማኅበሩ ርዕስ ክቡር ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው (በዝነኛውአልሞትኩም ብዬ አልዋሽምድርሰታቸው ይታወቃሉ) ሲሆኑ ቀጥለውም ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ማሕበሩን መርተዋል። ብላታ ጌታዬ አስፋው ተፈራ በጸሐፊነት ተመርጠው አገልግለዋል።
ማኅበሩን በልዩ-ልዩ ሥልጣነ-ወንበር ካገለገሉት ሌሎች ደግሞ በከፊሉ፦ አቶ አምደ ሚካኤል ደሳለኝ፣ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ አሰፋ ገብረ ማርያም፣ ደበበ ሰይፉማሞ ውድነህ እና አሁን በፕሬዝዳንትነት እየመሩት ያሉት ጌታቸው በለጠም ይገኙበታል።

"የኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር (ኢደማ) ተብሎ የተቋቋመው ይህ ድርጅት፣ መጠሪያውን 1970 .. ወደየኢትዮጵያ ደራስያን አንድነት ማኅበርከለወጠው በኋላ፣ ያሁኑን መደበኛ መጠሪያውንየኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር” (ኢደማ) ያገኘው የካቲት 11 ቀን 1978 .. ነው።

በቅርቡ "ፍኖተ ነፃነት" ጋዜጣ ላይ ማኅበሩን ከመሠረቱት እና በጸሐፊነትም ካገለገሉት ከብላታ ጌታዬ አስፋው ተፈራ ጋር በተደረገ ቃለ-ምልልስ እንደተዘገበው፤- ማሕብሩ ሲመሠረት በዋናነት ዓላማው አድርጎ የተነሣው «በሀገሪቷ ያሉት የጽሑፍ ቅርሶች በዋናነት ተሰባስበው እንዲታተሙና ሌሎች አዳዲስ ጸሐፍትን ለማፍራት» እንደነበር እና «የአሁኑ የሀገሪቷ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የደራስያን ማኅበሩ ገንዘብ ያዥ በነበሩበት ጊዜ መንግሥት የመጽሐፍ ህትመትን ወጪ ¼ እንዲሸፍን» አድረገዋል። ብላታ ጌታዬ አስፋው ቀጥለውም፣ «ይኸንኑ ¼ መንግሥት ይሸፍነዋል የሚባለውን ወጪ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሕትመቱን ካከናወነ በኋላ ያልተሸጠውን ትምህርት ሚኒስቴር እንዲገዛው ተደርጐ ትምህርት ቤቶች ለሪፈረንስ (ማጣቀሻ) እንዲጠቀሙበት ይደረጋል።» ብለዋል።

 
ንጉሠ ነገሥቱም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ «ለመጽሐፍ ትልቅ ፍቅር ስለነበራቸውና አርአያ ለመሆን ቲያትርን እንደሚመለከቱና እንደሚገመግሙ ሁሉ ወመዘክር (ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና መጽሐፍት ማዕከል) በመገኘት በመጽሐፍ ሂስና ውይይት ላይ ይካፈሉ እንደነበር» ብላታ ጌታዬ አስፋው ተፈራ ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ የብላታ ጌታዬ ትውስታ፣ በዘመኑ « .... ኃላፊ የነበሩት ክቡር አቶ አካለ ወርቅ ሀብተ ወልድ ፓሪስ ለስብሰባ በተገኙበት ጊዜ ሀገራችን በየዓመቱ 40ሺ ዶላር ለመክፈል በመስማማት ግዴታዋን ስትወጣ በአንፃሩም በአባልነታቸው በርካታ መጽሐፎችን ያገኙ እንደነበር ይመሰክራሉ» ይላል።

 
እሴቶች


የአባላት ደራስያንን ሥራዎች ለኅትመት እንዲበቁ ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ኹኔታዎችን ከሚፈጥርባቸው ነገሮች አንዱ ከማተሚያ ቤቶች ጋራ ያለው የሥራ ትብብር እና ስምምነት ነው። በዚህም ረገድ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት በተገኘ የ፪መቶ ፶ሺ ብርተዘዋዋሪ ድጎማአያሌ የተለማማጅ እና አንጋፋ ደራስያንን እና ገጣምያንን ሥራዎች ለኅትመት እንዲበቁ አድርጓል። ተመሳሳይ ስምምነቶችም ብርሃን እና ሰላም እንዲሁም ብራና ማተሚያ ቤቶች ጋራም እንደተደረጉ ተዘግቧል። ማተሚያ ቤቶቹ በጥሬ ገንዘብ የሚሰጡት ብር ባይኖርም ከኢ... ጋራ እስከ ተስማሙበት የገንዘብ መጠን ድረስ ከማኅበሩ ገምጋሚ ኮሚቴ አልፈው የሚመጡትን የአባላቱን ረቂቆች በነጻ ያትማሉ።
በማኅበሩ የሥራ ደንብ፣ የአንድ ደራሲ ረቂቅ የገምጋሚ ኮሚቴውን ምዘና አልፎ፤ አርትኦቱ ተሠርቶ እና ታትሞ ለገበያ ከቀረበ በኋላ ከሚያገኘው ትርፍ ላይ የአርትኦት ክፍሎ፣ ለማተሚያ ቤቱ እና ለኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር የተወሰነ ክፍያ የማድረግ ግዴታ ይኖርበታል።

... ካከወናቸው ዐበይት ተግባራት አንዱ 2002 .. የተከበረውን 50 ዓመት የወርቅ በዓል አጋጣሚ በማድረግና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በማስተባበር ሀዲስ አለማየሁ ከበደ ሚካኤል በሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን እና ስንዱ ገብሩ ምስል ያሳተማቸው የመታሠቢያ ቴምብሮች አንዱ ነው። በዚህ ትብብርየኢትዮጵያ ደራስያን ፪ኛ ዕትምበሚል የታተሙትና ጳጉሜ 2 ቀን 2004 .. አዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የተመረቁት ቴምብሮች ደግም ደራስያን ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ቀኝ-ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ እና አቶ ተመስገን ገብሬ ናቸው። የቴምብሮቹ ምስሎች የተነደፉት በአገኘሁ አዳነና እሸቱ ጥሩነህ ሲሆን፤ የ20 ሳንቲም፣ 80 ሳንቲም፣ የአንድና ሁለት ብር ዋጋ አላቸው።

 
 እነዚህ አንጋፋ ደራሲያን በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ እና ዘላለማዊ አሻራ የተዉ ናቸው፡፡


የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በግማሽ ምዕተ ዓመት ሕይወቱ ጊዜያት በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። አቋሙ ዘለቄታ ባለው መልክ እንዲቀጥል ለማድረግ የመጀመርያው ፕሬዝዳንት የነበሩት አርዐያእናየኤደኑ ጃንደረባመጻሕፍት ደራሲ ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት በጊዜው በብሔራዊ ቴአትር ለተወሰነ ጊዜ ከታየውቴዎድሮስከተሰኘው ተውኔታቸው ገቢ ላይ ፲ሺ ብር ለማኅበሩ ለግሰው እንደነበር ተዘግቧል። ሆኖም፣ ማኅበሩ በገንዘብ አቅሙ የጠነከረ ስላልነበረ በተለያዩ ጊዜያት የሥራ ክንውኑን ያልቀለጠፈ እንዳደረገው ይነገራል። ደራሲ ማሞ ውድነህ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት የአባላቱ ቁጥር አነስተኛነትና የገቢ ምንጮቹ ደካማነት የጽሕፈት ቤቱን የቤት ኪራይ እንኳን በአግባቡ እንዳይከፍል እስከማድረግ ደርሶ ነበር።


1997 .. ጌታቸው በለጠን ጨምሮ አዲስ የሥራ አስፈፃሚ ቡድን ከተመረጠ በኋላ ባሉት ጊዜያት ግን የሞያ ማኅበሩ በእጅጉ እየተቀየረ መምጣቱም ይነገራል። አዲሱ የሥራ አስፈጻሚ ለብዙ ዓመታት አዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረውን ጽሕፈት በአጭር ጊዜ እንዲስፋፋ አድርጓል። ማኅበሩ ዛሬ ሐረር ባሕር-ዳር ደሴ ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ ተጨማሪ ቅርንጫፍ /ቤቶች አሉት። የገቢ ምንጮቹንም በተለያየ መንገድ እያሰፋ ነው። ማኅበሩ የአባልነት መሥፈርት ብሎ ያስቀመጣቸው እንደ መጽሐፍ ማሳተም እና ለኅትመት ታስቦ የተጠናቀቀ ረቂቅ ጽሑፍ መኖርን ነው። በተለያዩ የኅትመት ውጤቶች ላይ ጽሑፍ የሚያቀርቡ ጸሐፍትም አባል መኾን የሚችሉበትን መስፈርትም አካቷል። እነዚህን መስፈርቶች ማሟላት የማይችል ነገር ግን አባል የመኾን ፍላጎት ያለውን ሰው ደግሞ ወርኀዊ ክፍያ እንዲከፍል በማድረግ በደጋፊ አባልነት እንዲቀጥል የሚያስችል ምቹ ኹኔታ አለው።



ብሌንመጽሔት


ብሌን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ይፋዊ ልሳን ነች፡፡ ይች መጽሔት የመጀመሪያ ዕትሟን ገጣሚ እና ደራሲ ደበበ ሰይፉ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሳለ ነሐሴ ወር 1982 .. ለንባብ ያበቃች ሲሆን እስከ ማኅበሩ 50 ኛው የወርቅ ዓመት ድረስ በሃያ ዓመታት በጠቅላላው ስድስት ዕትሞችን ብቻ ነው ያስነበበችው። በአዲስ ነገር ድር-ገጽ ላይ፣የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከተኛበት እየነቃ ነውበሚል ርዕስ በቀረበው መጣጥፍ እይታ የዚች ብሌንመጽሔት ወቅታዊነት ብቻ ሳይሆን በአቀራረብ «ዐምዶቿም ተከታታይነት እና ወጥነት አልነበራቸውም» እንዲሁም «ይህ ዐይነቱ አቀራረብ እና ብዙዎች ተወዳጅ አካሄድ ብለው የወሰዱት በኋላ ላይ በታተሙት የብሌን መጽሔቶች ላይ መደገም አልቻለም። አንዳንዶች መጽሔቷ በሥነ ጽሑፋዊ ብስለት እያሽቆለቆለች መጥታለች ሲሉ ትችት ያቀርቡባታል። የዐምድ መለዋወጡንም እንደ ዋነኛ ችግር የሚያነሱ አልታጡም።» በማለት ይተቻል።


ዋቢ ምንጮች
·         ሪፖርተር Ethiopian Reporter, ኪንና ባሕል፣ የካቲት 10 ቀን ፳፻፪ ..
·         AddisNeger Online, “የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከተኛበት እየነቃ ነው
·         ፍኖተ ነፃነት፤ ፪ኛ ዓመት ቅጽ. .፰፤ " የፈለቀች አርቲስት -“የፍቅር ጮራደራሲ ማነው? ማክሰኞ መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፬ ..


"