Sunday, January 28, 2018

አሁን አይኔ አየ ….የቴዲ አፍሮ የፍቅር ክታብ !

አሁን አይኔ አየ ….የቴዲ አፍሮ የፍቅር ክታብ !

(አሌክስ አብርሃም)


ቴዲ አፍሮ ግጥምና ዜማ አቀናጅቶ የሚዘፍን ድምፃዊ ብቻ አይደለምቴዲ የነበረውን ታሪክ እየመዘዘ በጎውን ይበል .. መጥፎውንም እንዳይደገም እያለ ከታሪክ ማህደር እኛነታችንን የሚተርክ ንቡር ጠቃሽ ነው ብያችሁ ነበርግን ይሄንንም ብቻ አይደለምልጁ ከውብ ሴት እግር ስር ተንበርክኮ ‹‹አንች ጋር አድሬ ሲነጋ ልሙት›› አይነት አልፎ ሂያጅ ፍቅር ሰባኪ አይደለምቴዲ ለእኔ ፈላስፋም ጭምር ነውቀላል ይፈላሰፋል! ያውም ነብስያችን ላይ ነዋ!! በቀደመው ፅሁፌ ‹‹የቴዲ ገፀ ባህሪያት ተራ ሰዎች አይደሉም ለአገራቸው የሚጠበቅባቸውን በሚገባ የተወጡ ምጡቅ ሃላፊነት የሚሰማቸው ነፍሳት ናቸው ›› ብያችሁ ነበርአሁን አንዷን ገፀ ባህሪ መዝዠ ለዚህ አባባሌ እማኝ ላቀርባት ነው …. በሉ ሙዚቃዋን ከፍ አድርጓትና ጨዋታችንን እንዲህ እንቀጥለው . . .
በመጀመሪያ ምደርም ባዶ ነበረ ጨለማም በባዶው ላይ እንዲል ቅዱስ መፅሃፉ የሰው ልጅ ሲፈጠር ባዶ ነውሲጀመር የወላጅ ድጋፍ ሲቆይም የቤተሰቡየጎረቤቱየመንደሩ ….የአገሩ ፍቅር እንደእህል ውሃ በውስጡ ህያውነትን እየገነባ ያሳድገዋልየሰውን ልጅ ሰፊ ባዶነት መሙላት የሚችል ብቸኛ ተአምር ፍቅር ብቻ ነው ! ሰዎች እየተናቆሩ እየተናከሱ እንኳን አብረው የሚኖሩበትን ከተማ ይመሰርታሉ ለሰው መድሃኒቱ ሰው የመሆኑ ሚስጥር የነፍስያ ሃቅ እንጅ ባዶ ፍልስፍና ወይም አባባል አይደለምና !!
ዛሬ ለእኔ የምንግዜም ምርጥ ፍልስፍና የሆነውን የቴዲ አፍሮ አንድ ዘፈን እንደሰማሁት ላሰማችሁ ይሄው ነገሬን ከስሩ ጀመርኩት ! ከዘፍጥረት!! ለምን ከዘፍጥረት ….ነገሩ ወዲህ ነው !
ጥንት እዚህ ባቡር ጣቢያው ከፍ ብሎ ካሉት ጭርንቁስ መንደሮች በአንዱ አንድ ድንቡሽ ያለ አይነ ስውር ህፃን ልጅነጭ ብትሩን ይዞ ከጨርቅ የተሰራች የደብተር መያዣ ኮሮጆውን አንግቶባቡር መምጣትና አለመምጣቱን በንቁ ጆሮዎቹ አጣርቶ ሃዲዷን ተሸግሮ ወደትምህርት ቤት ይሄድ ነበርታዲያ እሱ አለሙን ሁሉ ነጭ ይሁን ጥቁር ባይመለከትም ምንጊዜም ከኋላው የእናቱ አይኖች እንደመልአክ ክንፍ ተዘርግተው ይከተሉት ነበር …. ከእናት ፍቅር ከሚመነጭ ጾለት ጋር! ህፃኑ እየራቀ... እየራቀ ከእናቱ እይታ ሲሰዎር ግን ሰፊው አለም ውስጥ ማንም የለውምብቸኛ ህፃን ነውየህፃናት ጨዋታ ይሰማዋል ….ኳስ እየጠለዙእተሯሯጡ ….አይነስውር ነውና የህፃን ልቡ እንደልጆቹ መቦረቅ ባለመቻሉ ክፉኛ እያዘነች ጥጉን ይዞና ምርኩዙን አቅፎ አለሙን በጆሮው ልክ እየሰፈረ በብቸኝበት ይኖር ነበር ….
ይህን ህፃን በስሙ እንኳን የሚያውቀው ሰው አልነበረም ….በቃ ማንም ሰው ስለዚህ ሚስኪን ልጅ የሚያወራ ጉዳይ ካለው ‹‹ባለምርኩዙ ልጅ ›› እያለ ያወራል አገር የሚውቀው ከሰውነቱ በላይበነጭ ምርኩዙ ነበርአንዳንዴ ጉድለታችን አይደል መታወቂያችን ….ከጉድለታችን አሸግረው ሙላታችንን የሚታዘቡ ጥቂቶች በጣም ጥቂቶች ናቸው ! እንዲህ ይለዋል ቴዲ በውብ ዜማና ግጥሙ የነበረውን ሲተርከው …..
አይኖቸ አያዩ ብርሃን የላቸው
በልጅነቴ ድሮ አጥቻቸው . . . .
ልቤን ተሰማው እንግዳ ነገር
ምርኩዝ ይዠ ነው የሚያውቀኝ አገር
እናም በእነዚህ የብቸኝነት ምልልሶችበእነዚህ ከባድ የጨለማ ዘመኖች በእነዚህ የመገፋት ዘመኖች ….በአንዱ ቀን ይህችው ብቻዋን ጭል ጭል የምትል የህይዎት ብርሃን እናቱ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሞት ተለየችው …..አሁን ጨለማው ሙሉ ሆነ ድቅድቅ ጨለማ !! ማሙሽ በአካልም በስነልቦናም በጨለማው ውስጥ አደገ ! በዚህ ጉዞው ውስጥ ብቸኛ በዚች አለም ያለችው ዘመዱ የቅርብ ወዳጁ ምርኩዙ ብቻ ነበረች !! ከፊቱ ቀድማ እሱም ዳናዋን የሚከተላት አጋሩ !!

የብቸኝነት ጎምዛዛ ጣእም አፉ ላይ ይሰማው ጀመርየችግሩ ግዝፈት ከማህበረሰቡ አመለካከት ጋር ተዳምሮ የአእምሮውን ጓዳ በጭንቀትና በመራር እውነት ሞላው ….በእርግጥም ሁሉም ነገር ጨለማ ነበርይህን ግዙፍ ጨለማ ከምን ጋር እናወዳድረውገና ከዘፍጥረት ምድር ስትፈጠር ለብሳው ከነበረው ጨለማ ጋር ….በትክክል!! ….እናም ድምፃዊው በአደባባይ ‹‹ፍቅር እግዚአብሔር ነው ›› አላለም …?? ይሄው ልክ ሲመጣ ….እግዚሃር ደግሞ ብርሃን ነው ይላል መፅሃፉእናም በዘፍጥረት …. የፍቅር አምላክ ከላይ ከሰማይ የፈጠራትን ምድር ሲቃኝ እማይበጃችሁ ይጨልምበት ጥቅጥቅ ያለች ጨለማ …!! እግዚአብሔር ፍጥረት ጨለማ ውስጥ ሲቀመጥ አይወድምሁላችንም በብርሃን እንመላለስ ዘንድ ፈቃዱ ነውና እንዲህ አለ ‹‹ብርሃን ይሁን ›› ቃሉን ተከትሎ አለም በብርሃን ተጥለቀለቀች ይሄው እስከዛሬ ቀን በፀሃይ ማታም በጨረቃ ብርሃን ከምድር ተለይቶ አያውቅም ! እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን ካለ ዘላለማዊ ብርሃን ነውና !!
ወደቴዲ ገፀ ባህሪ እንመለስና የነገራችንን ውል ከዘፍጥረት ምሳሊያችን እናገናኘው ….ያች የህፃኑ ሚስኪን እናት ልትሞት ስታጣጥር ለልጇ በምድር ላይ ካሉት ነገሮች ሁሉ ከፍ ለውን ነገር ያገኝ ዘንድ መርቃው የመጨረሻ እስትንፋሷን ሳበች በቃ! ደሃ እናት ለልጇ ልታወርሰው ምትችለው የመጨረሻ ነገር የልብ ፍቅርና ምርቃቷል አይደል ..እሱን አወረሰችው ….ዘፋቡ እንዲህ ይለናል ስረፍቅር ውርሱ ወዲህም ስለእናቱ ምርቃት ነጆሮው የሰማውን ቃል ስምረት ሲያስረዳን
መሽቶ አይኔ በልጅነቴ
መርቃኝ ስትሞት እናቴ
በፍቅር ብራ እንዳለችኝ
አንች ላይ ወስዳ ጣለችኝ !! 
ይሄዋ እናቱ የመጨረሻ ምርቃት ‹‹በፍቅር ብራ ›› የሚል ነበርይች ብልህ እናት በጨለማ ውስጥ ተፈጥረው በጨለማ ውስጥ ቢያድጉም እንኳን በፍቅር መብራት እንደሚቻል ጠንቅቃ ያወቀች ነበረችእናም ምርቃቷን በመነመነ የመጨረሻ ትንፋሽ ወደልጇ ተኮሰችው ‹‹በፍቅር ብራ›› እግዜሩ ከሰማየ ሰማይ ይችን ምርቃት ሰማ እናም እንዲህ አለው ለዚህ በጨለማ ለኖረ ልጅ ‹‹ብርሃን በህይወትህ ላይ ይሁን ›› ….ቦግ አለ ወዲው !! እግዜር ነዋ ተናጋሪው ! ህፃኑ ወዲያው አለምን ወለል አድርጎ ተመለከታት ከነስንክሳሯ ከነውበቷ ….ከነመልካም ነገሮቿ ….እንዴት አለምን አየአይነስውር ነው አላልክምብለሁ!! እና የስጋ አይኑ በራለትአልበራም!! እና ….እናማ አየ በቃ ማየት ቻለፀሃይ አልነበረም ብርሃኑ ጨረቃም አልነበርልክ እንደእናቱ ምርቃት የፍቅር ብርሃን ከነፍሱ ጥግ ቦግ ብሎ በራ !! እናም ዘፋኙ ምርኩዙን አስቀምጦ በደስታ እንዲህ አለ ….
የምየ ሰምሮ ትንቢቷ
ወዳጅ አገኘሁ ካንጀቷ
ኩራዜን እንዲህ እንደማይ
አንች ነሽ ላምባዲናየ
አሁን አይኔ አየ!!!!!
ይሄው ነው የብርሃኑ ምንጭ የምትወደው ከምርኩዙ አልፋ በእሱነቱ የምታውቀው የነፍስ ፍቅረኛ አሻረው (ሰጠው ያንሳል ቃሉ) እናም ይሄ ወጣት በራለትበርቶለት ብቻ አልቀረም የዘመናት ብቸኝነቱ ውስጥ ውስጡ የተጠራቀመው እውነት በፍቅር ክብሪት ተለኮሰና እንደርችት በውብ ብርሃኑ ወደውጭ በዙሪው ወዳሉ ሁሉ ይረጭ ጀመረፍቅርን ሰበከውእኛም ሰማን እንዲህ ይላል ድምፃዊውላምባዲና በሆነችለት ውብ ነፍስ ላይ ተደላድሎ አይናማ ነን ብለው ለሚኮፈስቱ ሁሉፍቅርን ወደልብ ካላንቆረቆረ በስተቀር ይሄን ለምልክት የተቀመጠ አይንህን እንዳትኮራበትፍቅር የሌለው አይናማ ዛሬም በጨለማ ውስጥ እየተደናበረ ነው ….የአለም ብርሃን አንድ እሱም ፍቅር ብቻ ነው !! ከውድ አምፖሎች በሚመነጭ የኤሌክትሪክ ብርሃን የተሸቆተቆጠ ሳሎን ውስጥ ብትኖርም ቅሉ ፍቅር ልብህ ውጥ ከሌለ ተበላህ ጓድቦግ ያለ ጨለማ ውስጥ ነህቦግ ያለ ጨለማ !! ስንቱ መሰለህ አይኑ አፍጥጦ ፍቅር በእግሩ ስር ሲልፍ የማይታየውይሄ ነው መታወር ! ይለናል ድምፃዊውእንዲህ በዜማ
እንዳትኮራበት አይንህን
ፍቅር ያልነካው ልብህን
ይገርማል ብለን ልንሄድ ስንነሳቆይ አልጨረስኩም …. ምን ቀረ ስንል
በማየት ስለማትበልጠኝ
መነፅሬን ለውጠኝ ! ኧረ ምርኩዙንም ይውሰድ እኛ ደግሞ !ሃሃ ነዋ ...ስንቱ ነው ፍቅር አልታው ብሎ ወይም ፍቅር የሚመስል ሞቅታ ተከትሎ ገደል የገባእህ ብትል ግማሹ ህዝብ ከገባበት ገደል እስካሁንም አልወጣም አንዱ በአንዱ ላይ እዛው እየተነባበረእና የፍቅር ምርኩዝ ከማቀበል የበለጠ በጎነት ከየት ይመጣል! ያዝ ይሄን ምርኩዝ ጀመዓው !! እንዲያ ነው ፍልስፍናው ለኔ!!
ፍቅር የሌለው አይናማ
ውጦታልና ጨለማ !!
ሰው ወዶ ሰው ያልወደደው
መርኩዜን መጥቶ ይውሰደው !! ይልሃል ቴዲ !ሃቅ ነው እንላለን እኛም !!በተወደድነው ልክ እንደውም በቻልነው መጠን ብንወድ ምን ይጎድልበናል አቃቂር እያወጣን ጉድለት እያፈላለግን ከመጥላት የነብስያ መቀጨጭ እና በጫጨት እንጅ ድሎት አይገኝ !! ውሰዱ ብለናል የፍቅር ምርኩዝ (እንደውም ማስታወቂያ ….አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ ለመላው የሰው ልጅ የፍቅር ምርኩዝ በዚህ ይገኛል ….በቅናሽ ሳይሆን በነፃተጦሃርቶ መምጣት ነው ዋጋው ) ማነህ ይሄን ማስታወቂያ ከዳር እስከዳር በዘጠና ሚሊየን ኮፒ አባዝተህ ለጥፍልኝ !!
ያይኔ መቅረዙ ባዶ ነው
ማየት ለብቻው ምንድነው
ሳያይ ያመነ ሲጠራው
እይ ፍቅር መጥቶ ሲያበራው !! አሜን እንል ዘንዳ እዚህ እንገደዳለን !!
አሁን አየ አይኔ …….እንግዲህ እኔም የቴዲን ላምባዲና እንደበራልኝ ወደእናተ አመጣሁትእንዲህ ሲዘፈን እንዲህ ብንሰማ አይፈረድብንማኪነጥበብ የነፍስ ሃቅ ነው አላልንም ….ኪነጥበብ ቤት መምታት ሳይሆን በእያንዳንዱ ሰው ቤት ውስጥ መግባት ነው አላልንምለዛ ነው ለተዲ በራችንን ከፍተን ያስገባነው እንላለን ወደፊት ለሚመጡም የመወደዱ ሚስጢርም አልገባንም ላሉ ሁሉ !! በነገራችን ላይ ላምባዲና ታውቃላችሁለማታውቁ በጣም በድሮ ጊዜ ውስጡ ላምባ የሚሞላበት እንደኩራዝ አይነት ቤት ውስጥ ለመብራትነት የሚጠቀሙበት ቆርቆሮ ነበርየእጅ ባትር በሚኒሊክ ዘመን ሲመጣ ስያሜው ለእጅ ባትሪ ተላለፈ ….በገጠር ወንድ ልጅ የእጅ ባትሪውን ከእጁ አይለይም መሪው ናትለአደጋ ጊዜ ተግ የሚያደርጋት ጨለማውን መግፈፊያው ናትቴዲ ላምባዲና ሲላት ፍቅሩን እውነት አለው !!
አለም ታየችኝ ባንች ውስጥ ሁና
በፍቅር ኩራዝ በላምባዲና !!
Alex Abreham በነገራችን - ላይ
#TeddyafroEthipia
ፍቅር ያሸንፋል!!