Friday, January 26, 2018

ቅድስት ድንግል ማሪያም

ቅድስት ድንግል ማሪያም 
ከ ‹‹ታማልዳለች›› እና ‹‹አታማልድም ›› በፊት 
( አሌክስ አብርሃም )
የስነ - መለኮት ትምህርት የሚማር ጓደኛየ ‹‹ስለ ድንግል ማሪያም ምድራዊ ቆይታ በአማርኛ የተፃፉ መፅሃፍትን ላክልኝ ›› ስላለኝ በርካታ መንፈሳዊ መፅሃፍ የሚሸጥባቸው ቦታወች ዞር ዞር ብየ የተባልኩትን መፅሃፍ መፈለግ ያዝኩ ! ማግኘት የቻልኩት ግን ከሁለት መፅሃፍት አይበልጡም ! ( በደንብ ባትፈልግ ነው ሞልቷል ትሉኝ ይሆናል ) እውነቱን ለመናገር በራሴም ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ባላቸው ሰወችም ባስፈልግም የተባለው መፅሃፍ እንኳን ሊሞላ ከጠቀስኩት ቁጥር ከፍ ማለት አልቻለም !!
በጣም ነው የገረመኝ … ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ስለ ሃዋሪያት ፃድቃን ሰማእታት ፣ መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ስማቸው ስለተጠቀሱ ሁሉ መፅሃፍት (በግለሰቦች የተፃፉ ረዳት መፃህፍት ) ገበያው ላይ ለጉድ ታገኛላችሁ . . . ስለድንግል ማሪያም ስትጠይቁ ግን የሚሰጧችሁ መፅሃፍ የሚበዛው በሁለት ፅንፍ ተወጥሮ ወደክርክር የሚያዘነብል ‹‹ማማለድና አለማማለድ›› ላይ ያተኮረ ይዘት ያለው መፅሃፍ ነው ! ለዛውም ራሱን ችሎ ስለድንግል ማሪያም የተፃፈው መፅሃፍ በጣም ትንሽ ነው ‹‹የማማለድና ያለማማለድ ›› ይዘት ያላቸው ቁንፅል ታሪኮች ስለሌሎች መንፈሳዊ ጉዳዮች በተፃፉ መፅሃፍት እንደአንድ ርእስ ሸጎጥ ተደርገው ነው የሚገኙት ! (እስቲ ጎራ ብላችሁ ጠይቁና ታዘቡኝ )
ከዛ ቀን በኋላ ዝም ብየ ሳስብ አይምሮየ ውስጥ የሚመላለሰው ‹‹ ህፃናት ልጆች ስለማሪያም ምን ያስባሉ›› የሚል ጥያቄ ነበር ! ያብስራ የምትባል ፕሮቴስታንት ቤተሰቦች ያሏት ልጅ (አስር አመት ቢሆናት ነው ) አግኝቸ ጠየኳት
‹‹ ያብስራ ! ስለማሪያም የምታውቂውን ንገሪኝ እሰቲ ››
ትንሽ እንኳን ሳታስብ በቀጥታ እንዲህ አለችኝ ‹‹ ማሪያም አታማልድም ››
‹‹ መማለድ ምንድን ነው ››
‹‹እኔጃ !!››
ሆነ ብየ ተመሳሳይ እድሜ ላይ ያለ ህፃን ልጅ ቤተሰቦቹ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች የሆኑ ጥያቄን ደገምኩ
‹‹ ስለማሪያም የምታውቀውን ንገረኝ እስቲ …››
‹‹ማሪያም አማላጃችን ናት ›› አለኝ ቀስ ብሎ
‹‹ መማለድ ምንድን ነው ?›› አልኩት …መሬት መሬት እያየ ዝም ! እንደገና ስጠይቀው ትከሻውን ወደላይ ሰብቆ ምን እንደሆነ አለማወቁን ገለፀልኝ !!
ታዲያ ቅድስት ድንግል ማሪያም መፅሃፍ ቅዱስ ላይ የተፃፈውና ያሳለፈችው ታላቅ ምድራዊ ውጣ ውረድ ‹‹በታማልዳለችና በአታማልድም ›› የክርክር ደመና ተሸፍኖ ይህ ትውልድ ማወቅ የሚገባውን ታሪኳን መውሰድ ያለበትንም ትምህርት ሳያገኝ ቀርቷል የሚል የራሴ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ ! እንደውም እንእአኔ እምነት እና መረዳት የቅድስት ድንግል ማሪያም ምድራዊ ቆይታ ታሪክ በየትኛውም እምነት ላለ ሰው (በየትኛውም እምነት ለማያምንም ሰው ጭምር ) ትልቅ መልእክት ያለው እና መነገር ያለበት አስተምሮ ነው !!
ስለዚህ መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ከተፃፈው በመነሳት ቀጥሎ ያሉትን ነጥቦች ፅፊያለሁ (ይህ ፅሁፍ እንደአንድ የእምነት ተቋም ወይም እንደአንድ የሃይማኖት ሰባኪ መልእክት ሳይሆን አንድ ተራ ግለሰብ ያነበበውን ታሪክ በተረዳበት መንገድ እንዳስቀመጠው ተደርጎ ቢታይ መልካም ነው - የእኔ የግሌ አመለካከት ብቻ ነው ) እናም ስለድንግል ማሪያም ምድራዊ ቆይታ እንደሚከተለው ፅፊያለሁ ! በጉዳዩ ላይ ጥልቅ እውቀት ያላችሁ የበለጠ እንደምታብራሩልንና እንደምታስተምሩን ከፍ ያለ ተስፋ አለኝ …..
1 . ግጭት ከማህበረሰቡ ባህልና ወግ ጋር !
እንደ አይሁዶች ወግ አጥባቂ ህዝብ በምድር ላይ ያለ አይመስለኝም ! ስርአታቸው ብዛቱ ህጋቸው ከመንዛዛቱ ማስፈራቱ … በዛ ላይ የሰው ጥፋት ማጋነን ሲወዱ ! እንግዲህ በዚህ ህብረተሰብ ውስጥ አንዲት ሴት ካመነዘረች እጣ ፋንታዋ በድንጋይ ተወግሮ መሞት ነው ..ደግሞ በአይሁድ ስርአት ማንኛውም ሰው ሊያገባ ቃል ገብቶ ታማኝነቱን ቢያጎድል እንደአመንዝራ ይቆጠራል ! ምህረት የለም ! በዚህ …ነገርን እንደክር የሚፈትል የህግ መተላለፍን በንስር አይን በሚከታተል ህብረተሰብ መሃል አንዲት እራሷን ጠብቃ የሰውንም የፈጣሪንም ህግ አክብራ የምትኖር ድንግል ሴት አለች …ህብረተሰቡ ማሪያም ነው የሚላት !
ይች ጨዋ ሴት ታዲያ አንድ ቀን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በፊቷ ተገለጠና የመሃበረሰቡን ባህልና ወግ የሚደረማምስ የየትኛዋንም ድንግል ሴት ልብ የሚያርድ ነገር ተናገራት! መልእክቱ ባጭሩ ‹‹ ማሪያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ፀጋን አግኝተሸልና አትፍሪ ! እነሆ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ ……›› በማለት ከእርሷ የሚወለደው ልጅ ወደፊት ለአለም ሁሉ መዳን እንደሚሆን አበሰራት ….የማሪያም አስገራሚ ፅናትና እምነት የሚታየው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው . . .
ድንግል ሴት ወንድ አጠገቧ ድርሽ ብሎ የማያውቅ ሴት ‹‹ትፀንሻለሽ ›› ስትባል ምን ሊሰማ እንደሚችል አስቡት… ያውም እጮኛ ያላት ከብረት የከረረ ህግ ያለው አገር ውስጥ የምትኖር ! በጨዋነት ያሳደጉ ቤተሰቦቸ ምን ይሉኛል ….እጮኛየ አምኖኝ አረገዘች ቢባል ምን ይላል …ህብረተሰቡ ምን ይላል ….እነዚህ ነበሩ አስጨናቂወቹ ጉዳዮች ማሪያም ከጉዳዩ ይልቅ በእርሷ ሂወት ላይ የሚከተለውን መከራ አስባ ‹‹ ኧረ እኔ አልፈልግም አገር መንደሩ ምን ይላል ባይሆን ካገባሁ በኋላ …›› ምናምን አላለችም :: ነገር ግን ነገን አሻግራ ተመለከተች አለምን ‹‹የሚያድን ልጅ ›› ስለዚህ የራሷን ጉዳይ ተወችውና አሰራሩን ለማወቅ መልአኩን እንዲህ አለችው
‹‹ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል ? ›› መለአኩ እንዴት እንደሚሆን ነገራት ወንድ አጠገቧ ሳይደርስ መንፈስ ቅዱስ በእርሷ ላይ እንደሚመጣ የእግዚአበሄርም ሓይል ተአምሩን በእርሷ ላይ እንደሚሰራ አስረዳት . . . ይሄ ውስብስብ እና ከሰው ልጅ አይምሮ በላይ የሆነ አሰራር ከዛን ጊዜ ጀምሮ እስካሁንም አለምን ሲያነታርክ ሳይንስንም ሲያሳንሰው ኑሯል … ይች ድንግል ሴት ግን አንድ ነገር ገብቷታል . . . እንደማንኛውም አይሁዳዊ የእግዚአብሄርን ተአምር ሰምታለች ተምራለች ባህር መክፈሉ በምድረበዳ ኢስራኤልን በድንቅና ተአምር ማሳለፉ ይህን ሁሉ ጠንቅቃ ታውቃለች !
(በኋላ ወደኤልሳቤት ጋ ከሄደች በኋላ ያቀረበችውን ምስጋና ስንመለከት የእግዚአብሔርን ሃያልነት ምን ያህል ታውቀው እንደነበረ እንረዳለን ) ሁሉም ያገሩ ሰው ይሄን ያውቃል በቃሉም ሸምድዶታል ! ዋናው ነገር ግን ዛሬ ያ በታሪክ የሚታወቅ አምላክ ፊት ለፊት መለአኩን አቁሞ ከሰማችው እና ካየችው በላይ የባሰውን ተአምር ‹‹በአንች ላይ አደርጋለሁ›› ሲል አምኖ መቀበሉ ላይ ነው ! ተአምር ሰምቶ እልል ማለትማ ማንም ይላል …ራስ ላይ ይሆናል ሲባል ነው ልብ ወደኋላ የሚያፈገፍገው ! አስኪ አሁን እግዚአብሔር ባህር መክፈሉን ሰምተን ሁላችንም ‹‹ወይ ተአምር ›› ብለናል ግን አሁን የፊታችን ቅዳሜ አግዚአብሔር እዚች ጣና ሃይቅን ለሁለት እከፍለዋለሁ ብሎ ቢናገር ስንቶቻችን ነው ‹‹ በቃ ይከፍለዋል ›› ብለን በእርግጠኝነት ሳናይ የምናምነው … እሩቅ ነገርን ማመን ዛሬ ካለ እምነት የትየለሌ ልዩነት አለዋ !
እዩትላችሁ አንዴ ከሰማይ መና እየወረደለት አንዴ ከድንጋይ ውሃ እየፈለቀ ሌላ ጊዜ ባህር እየከፈለ ተአምሩን ልክ እንደሰርከስ ትርኢት በፊታቸው ያሳያቸው እስራኤላዊያን ወገኖቿ እንኳን የእግዚአብሄርን ተአምር ለመቀበል ተቸግረው በየጊዜው እግዚአብሄርን ሲክዱ ሲመለሱ አርባ አመት ኑረዋል ! ይህች ሴት ግን በፊቷ ባህር አልተከፈለ መና አልወረደ ‹‹ አምላክሽ የሚሳነው የለም ለሰው የማይቻለውን እርሱ ማድረግ ይችላል ›› ስላላት ብቻ ቃሉን አምና እንዲህ አለች
‹‹እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደቃልህ ይሁንልኝ !! ››
የእምነት የመጨረሻው ጥግ ቃሉን ማመን ተፈፀመ !! በነገራችን ላይ እንደእኔ እውቀት እንደድንግል ማሪያም ፍፁም እምነት በእግዚአብሄር ላይ ያሳደረች ሴት በመፅሃፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የለችም ! ‹‹ከማማለድና ካለማማለድ ›› በፊት የቅድስት ድንግል ማሪያም ስም ሲነሳ ሳያዩ ማመን ፣ በእግዚአብሔር ቃል ፍፁም እምነት ማሳደር …. ከባህል ና ወግ ፣ ከእጮኛና ከቤተሰብ ከህግ እና ከራስ ክብር በላይ የእግዚአብሔርን ቃል ይሁን ብሎ በእምነት መቀበል የቅድስት ድንግል ማሪያም መገለጫ ነው !! እኛም መጀመሪያ ስለቅድስት ድንግል ማሪያም ስናስብ የማይናወጥ እምነት አብሮ ሊታወሰን ይገባል !
‹‹ እንደቃልህ ይሁንልኝ ›› ስትል ልጁን ፀንሸ ወልጀ አሳድጌ ለአለም ሁሉ መድሃኒት ሁኖ ….በሚል ጉጉት አልነበረም ….ከዚህ ሁሉ በፊት ሊከሰት የሚችለውን መከራ ለመቀበልም መወሰን እንጅ !! ስለቃልህ ቢወግሩኝ ይውገሩኝ ቢገድሉኝ ይግደሉኝ ፣ አገር ጉድ ቢል ይበል ቤተሰብ ስለእኔ ቢያፍር ይፈር እጮኛ ትቶኝ ቢሄድ አልያም ቢከሰኝ ይክሰሰኝ ! ማለት እኮ ነው ! ከአንዲት ድንግል እና ምድራዊውን መከራ ትከላከልበት ሰዋዊ አቅም ከሌላት ሴት እንዲህ አይነት ድፍረት እና እምነት የተሞላ ልብ ይገኛል ብሎ የሚገምት ሰው አይኖርም ፡፡ ይች ሴት ግን ብቻዋን በልቧ የአምላኳን ቃል ቋጥራ ከግዙፉ የማህበረሰብ ባህልና ወግ ጋር ተጋጨች !
2. ግጭት ከመንግስት ጋር
ማሪያም በሚያከብራት እጮኛዋ ነበር መጀመሪያ ዝቅ ተደርጋ የታየችው . . .ፃዲቅ ስለነበር ለሰው ሊያጋልጣት አልፈለገም (የሰው የመጨረሻው አክብሮት ቢበዛ ለሰው አሳልፎ ሳይሰጥ ብቻውን በልቡ መናቅ ነው ) እናም ዮሴፍ በልቡ ማሪያምን ታዝቧት ካስቀመጠባትም ክብር ዝቅ አድርጎ እዛው እንደፍጥርጥርሽ ብሎ ጥሏት ሊሄድ ሲል ማሪያም ‹‹ እንዴት መሰለህ እኔ ከማንም ጋር አልሄድኩም ታማኝ ጨዋ ነኝ እመነኝ እግዚአብሔር መርጦኝ ምናምን ›› አላለችም ታላቁን እውነት ሚስጥሯን በልቧ ይዛ ዝም !
አላወራችም ለማንም ! ‹‹አለምን የሚያንቀጠቅጥ ልጅ እኮ ነው ያረገዝኩት ምናምን ›› አላለችም ! ዝም ! ይታያችሁ በዛ ዘመን የነበሩ ሴቶች አንዳንዶቹ በጉባኤ መሃል ጩኸታቸው እየረበሸ ‹‹ኧረ ዝም በሉ›› የሚባሉ ነበሩ …. ደግሞ ኢየሱስ በተወለደበት እና ነብዩ ሚሊኪያስ በሞተበት መሃል የነበረው ዘመን ብልግናው ርኩሰቱ ስርዓት አልበኝነቱ የተጧጧፈበት ሰወች ቃላቸውን የሚያጥፉበት ውሸት ማመንዘር ‹ፋሽን › የሆነበት አደገኛ ዘመን ነበር ….
በዚህ መጥፎ ዘመን ነው ….ይች ድንግል ሴት ይሄን የሚያክል ሚስጥር በልቧ ጠብቃ ዝም ያለችው ! ልሳኗ ቃል የገባላት አምላኳ ነበር …እናም ዮሴፍ ሊሄድ መንገድ ሲጀምር እግዚአብሄር በህልሙ ተከሰተና ‹‹ ወዴት ነው ? ጉደዩ ምድራዊ አይደለም ወዲህ ነው ነገሩ ዮሴፍ ሆይ ተመለስ ! ይች ሴት ጨዋ ናት ማንም ነክቷት አያውቅም ፣ ይች ሴት ትሁት ናት ከእምነቷ ዝንፍ አላለችም ፣ ይች ሴት ከአለም ሴቶች ሁሉ እኔ ለታላቅ ስራ የመረጥኳት ብፅእት ናት ቅድስት ናትና ተ መ ለ ስ !›› አለው !
ጉዞ ወደቤተልሔም ዳዊት ወደተወለደባት ከተማ ሆነ …. ማሪያምና ዮሴፍ ገሊላ ክፍለሀገር ናዝሬት የምትባል ከተማ ቢሆንም ኑሯቸው የዳዊት ዘር ስለነበሩ ለህዝብ ቆጠራ ወደ ዳዊት የትውልድ ቦታ ቤተልሔም ሄዱ . . . ያው ቤተልሔም ምኝታው ሁሉ ለቆጠራው በሄደው ህዝብ ተይዞ ስለነበር ማሪያም በበጎች ግርግም አረፈች . . . የሚድኑት ቦታውን ይዘውት አዳኙ በበግ ጋጣ ተወለደ …መወለዱን በመልአክ የተበሰሩት እረኞች ነጉስ ተወልዷል ሲባሉ የዘመኑ ንጉስ ወዳለበት ቤተመንግስት ሂደው ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉስ የታለ ›› ብለውት እርፍ ! ንጉሱ የክፋት ሰይፉን መዘዘዋ … አሁን ጉዳዩ የስልጣን ጦርነት ሁኖ አረፈ ….እድሜው ከ ሁለት አመት በታች የሆነውን ህፃን ሁሉ በወታደሮቹ አስጨፈጨፈ …ማሪያም በዚህ ጭፍጨፋ ውስጥ ምናይነት የነብስ ጭንቀት ውስጥ እንደምትሆን አስቡት !
ቀላል ምሳሌ እዚህ እኛ አገር ቀይ ሽብር ተብሎ ወጣቱ ሲፈጅ እናቶች አንጀታቸውን በመቀነት አስረው ልጆቻቸውን ይደብቁበት ቀዳዳ አጥተው በጭንቀት ሲንቆራጠጡ ኖሩ …በነገራችን ላይ ያ ሁሉ አመት አልፎ እንኳ በቀይ ሽብር ዘመን የነበሩ እናቶች ዛሬም ድረስ የመኪና ጎማ ሲፈነዳ ተኩሱ ትዝ እያላቸው ይበረግጋሉ ! እናትነት ሰቆቃ ነው !
እንገዲህ ድንግል ማሪያም ያውም በአዋጅ ልጇን ሊገድሉ የሚራወጡ ወታደሮች በሚራወጡበት አገር ምናይነት የእናትነት ስቃይ ውስጥ እንደምትሆን ማሰብ ይቻላል . . . ሁሌም ለቃሉ ታማኝ የሆነው አምላኳ ‹‹ ወደግብፅ ልጁን ይዛችሁ ሂዱ ›› ሲል ከመአቱ አወጣቸው . . .አስራ ሁለት ነገድ አርባ አመት በተጓዘበት መንገድ አንዲት ሴት ልጇን አቅፋ ዮሴፍንም አስከትላ የአምላኳን ትዛዝ በመቀበል ጉዞ ጀመረች . . . ምክንያት ንጉስ ወልዳለችና ከምድራዊው ንጉስ ጋር ተጋጭታለቻ !
ከህዝብ ባህልና ህግ ጋር ተጋጭታ ፣ ከመንግስት ጋር ተጋጭታ ልጇን እንዳቀፈች አምላኳን መሪ ቃሉንም ምርኩዝ ያደረገች አራስ ሴት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለማክበር እንደምጣድ በሚያንገብብ ምድረበዳ ላይ ተገኘች . . . ቅድስት ድንግል ማሪያም የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት ! ‹‹ከታማልዳለችና አታማልድም ›› ክርክር በፊት ስለእግዚአብሔር ቃል በፅናት መንከራተትና መሰደድን በእምነት ምድረበዳን መሻገርን ያስተማረች የእምነት ጥግ ናት . . .
ይሄ እንደውም ከሚመጣው የእናትነት ሰቆቃዋ ጋር ሲነፃፀር ምንም ማለት አልነበረም . . . ከየትኛዋም ምድራዊ እናት አይምሮ በላይ የሆነ ግፍና ሰቆቃ ከፊቷ እየጠበቃት ነበር …ነብዩ ሰምዖን ‹‹ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል ›› እዳላት . . .
በእርግጥም ድንግል ማሪያም በግርፋት ብዛት ቆዳው የተተለተለ ልጇ በደም አበላ ተውጦ ደረቅ እንጨት ላይ እርቃኑን በሚስማር ሲቸነከር ተወዳዳሪ የሌለው የሰቆቃ ስለታም ሰይፍ በነፍሷ እያለፈ . . . የእናትነት አንጀቷን በእምነቷ መቀነት አስራ በዛው ነበረች !!
የሚገርመው ነገር ደግሞ ‹‹በቃ አበቃ ተከተተ ልጅሽ ሞተ›› ከሚለው የተስፋ መቁረጥ መርዶ በላይ የገዘፈ እምነቷ …በታሪክ ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ ሞትን ድል አድርጎ እንደሚነሳ የተናገረ አምላኳን ትንሳኤ ከሚጠብቁት ሰወች መካከል የመጀመሪያዋ ራሷ ድንግል ማሪያም ነበረች . . . ‹‹ከታማልዳለችና አታማልድም›› ክርክሩ በፊት የእምነትን ፅናት ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ግፍና ሰቆቃን ችሎ በእምነት መፅናትን ለአለም ሁሉ በተግባር ያሳየች ብርቱ ሴት ቅድስት ድንግ ማሪያም ነበረች !!
ታላቅ ስሟ በታማልዳለችና አታማልድም የክርክር ደመና ተሸፍኖ ትውልድ ሊታነፅበት የሚችል ተወዳዳሪ የሌለው እምነቷ ፣ ትህትናዋ ፣ እናትነቷ ፣ ታጋሽነቷ እናም ምሳሌነቷ ሊነገር በሚገባው ልክ አልተነገረምና ጋሪውን ከፈረሱ ያስቀደማችሁ እናተ መምህራን ሆይ ለትውልዱ ታላቅ ስራዋን ከክርክር በነፃና ከጥላቻ በራቀ መንፈሳዊ ስርአት አሳውቁት ማማለድ አለማማለዷን ትውልዱ ራሱ ይናገር !!
መልካም የገና ሰሞን ከሚል ምኞት ጋር !

No comments:

Post a Comment