Friday, January 26, 2018

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ
አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ፣
አቃጥሎ ለብልቦ ፈጅቶ ገደላችሁ።በመሳፍንታዊው ዘመን ሳይጠበቅ ብቅ ያለውን መይሳው ካሣ/ ቴዎድሮስን አንዲት ተጎጂ አልቃሽ የገጠመችበት ስንኝ ነው፡፡

አንዷን ኢትዮጵያ ሰላሳ አርባና ሀምሳ ቦታ ቦጫጭቀው ለዕለት ደስታቸው የሚኖሩ መሳፍንት በበዙበት ዘመን አንድ ሰው ተወለደ፡፡ የዚህን ጀግና እትብት የቀረበረች ቋራ እንደምን የታደለች ናት፡፡ ቋራ ከዚያም ቀድሞ የጀግኖች ከዚያም በኋላ የጀግኖች ምድር ናት፡፡
የጥር ወርን በራፍ ታላቁን ምድር እያነሳን እንዘክረዋለን፡፡

አባ ታጠቅ ካሳ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከ1999 ዓመት በፊት ጥር 6 ቀን 1811 ዓ/ም በጎንደር ቋራ ተወለዱ፡፡ አባታቸው ደጃዝማች ሀይለጊዮርጊስ ከሱዳኖች ጋር በ 1813 ዓም ሲዋጉ በመሞታቸው እናታቸው አትጠገብ ወንድ በወሰን ከቋራ በመሸሽ ወደ ጎንደር ከተማ በሁለት ዓመታቸው ይዘዋቸው መጡ፡፡
ወይዘሮ አትጠገብ የጎንደር ከተማ መስራች የአፄ ፋሲለደስ ዘመድ ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ የጎንደር ባላባት ዘር ናቸው እንጂ በታሪክ እንደሚታወቀው ኮሶ ሻጭ አልነበሩም ፡፡ ነገር ግን አፄ ቴዎድሮስን ለማዋረድ የኮሶ ሻጭ ልጅ ሲሉ ጠላቶቻቸው ጠርተዋቸዋል (ጳውሎስ ኞኞ)
አፄ ቴዎድሮስ በእናታቸው ወገን ምንም ወንድም ሆነ እህት አልነበራቸውም ፡፡ እናታቸው ደጃዝማቹ ባለቤታቸው እንደሞቱ ወዲያው ቆርበው ስለነበር ሌላ ልጅ አልወለዱም፡፡ለዚህም ነው ቴዎድሮስ አንድ ለናቱ የተባሉት ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፤በትውልድ ስማቸው ካሳ ሀይሉ፤በውትድርና ስማቸው ደግሞ መይሳው ካሳ ሲባሉ የዙፋን ስማቸው ዳግማዊ ቴዎድሮስ ነው፡፡
በትውፊት እንደሚነገረው በ15 ኛው መቶ ክፍለዘመን ቀዳማዊ ቴዎድሮስ የተባለ ተወዳጅ ኢትዮጵያዊ ንጉስ ነበር ይባላል፡፡ ይህ ንጉስ በ19 ኛው መቶ ክፍለዘመን ዳግም ይመጣል ተብሎ በተነገረው ትንቢት መሠረት ካሳ ሀይሉ ራሳቸውን ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ ብለው የካቲት 11/1847 ዘውድ ደፉ፡፡
ቴዎድሮስ የሚለው ስያሜ ጣዎስ ድሮስ ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም የአምላክ ስጦታ ማለት ነው፡፡ ቴዎድሮስ ምናልባት መፅሀፍ ቅዱስን ደጋግመው ስላነበቡ የሽሩባቸው ምንጩ መፅሀፍ ቅዱስ ሊሆን ይችላል፡፡ በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ በሽሩባው ሀይልን የታደለ ሳምሶን የሚባል ሰው ነበርና፡፡በእርግጥ በቴዎድሮስ ዘመን ፀጉር ማሳደግ የጀግንነት ምልክት ነበር፡፡
አፄ ቴዎድሮስ አራት ጊዜ አግብተው 6 ወንድ፣3 ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ እነሱም( ራስ እንግዳ፣ራስ መሸሻ፣ሃይለማሪያም ፣አልጣሽ (የምኒልክ የመጀመሪያ ሚስት)፣ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ወዘተ) ሲሆኑ ብዙዎቹ በመቅደላ ጦርነት ላይ ወድቀዋል ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ወዳጆቼ የሚሏቸው ሩሲያ እና እንግሊዝ የግብጽ እና የቱርክ ወራሪዎችን ትንኮሳ እንዲያስታግሱላቸው በተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢፅፉላቸውም ምላሽ አጡ፡፡
ይልቁንም እንግሊዝ ከቱርክ ጋር በማበር ሩሲያን በክሪሚያ ጦርነት ወጋቻት፡፡
አፄ ቴዎድሮስም እልህ ተጋብተው በኢትዮጵያ የነበሩትን እንግሊዛዊያንን አስረው ሴባስቶፖል መድፍን አሰሩና ስያሜውን ለሩሲያ የጦር ሜዳ ሰጡ፡፡_( ባህሩ ዘውዴ)
አፄ ቴዎድሮስ በ 13 ዓመታት የንግስና ጊዜያቸው የባሪያ ንግድን፣ጎጠኝነትን፣ከወገብ በላይ ተራቁቶ የመጓዝ ባህልን. . . ወዘተ አስቀርተዋል፡፡
ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ቴዎድሮስ የወቅቱን ዘመናዊ ጦር፣ዘመናዊ የመከላከያ ምሽግ እና ዘመናዊ ሙዚየም አቋቁመዋል፡፡ ከውትድርናው ውጪ መፅሀፍ ቅዱስን በአማርኛ በብዛት እንዲተረጎም ከማድረግ ባለፈ ስነፁሁፍ እና ፍልስፍና እንዲያድግ የቻሉትን ያህል ጥረዋል፡፡
የመንገድ ዝርጋታ በማስጀመርም ሆነ ብሔራዊ ፍቅርን በመስበክ ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የአንድነት መነሻ ሆነዋል፡፡ (ፓውል ሄንዝ ) አጼ ቴዎድሮስ ብዙ የጓጉለትን ለውጥ ማምጣት ሳይችሉ ከውስጥና ከውጭ በተቀሰቀሰባቸው ተቃውሞ ምክኒያት የእንግሊዝ ወራሪ ጦርን ተፋልመው በሚያዝያ ወር 1860 ዓ.ም. መቅደላ አምባ ላይ ለሀገራቸው መስዋዕት ሆኑ፡፡ ከሞታቸው በኋላም ፡-
<መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ .
የሴቱን ባናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ › ተብሎ ተገጠመላቸው ፡፡ እንግሊዛዊያን በወቅቱ ቴዎድሮስን ለመውጋት 32 ሺ ዘመናዊ ወታደር ይዘው ወደ መቅደላ እንደመጡ ታሪክ ዘግቧል፡፡ የስልጣኔ ህልማቸውን ሳያሳኩ ያለፉት ዓጼ ቴዎድሮስ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን እየሰብኩ በዚች ምድር ላይ ለ49 ዓመታት ኖረዋል፡፡
ምንጭ
 አብመድ
 ጳውሎስ ኞኞ
 ባህሩ ዘውዴ
 ድሬ ትዩብ
 ልዩ ልዩ
 ምስል- ተፈሪ ምህረተ አብ -ዘ ታቦር

No comments:

Post a Comment