Friday, January 26, 2018

ነገረ - ፍልስፍና!

ነገረ - ፍልስፍና!
(እ.ብ.ይ.)

አንዳንድ ሠዎች ፍልስፍናን አርቀው ይመለከቱታል፡፡ ፍልስፍና ግን በቅርብ ከኑሯችን ጋር ተስማምቶ የሚኖር ነው፡፡ ፍልስፍና ጥያቄ ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ለጥያቄዎቹም መልስ ለማግኘት መታተር ነው፡፡ በዚህ ረገድ በሕይወታችን ጠይቀናቸው ያልተመለሱ ጥያቄዎች መልስ ካገኘንባቸው ይልቅ በእጅጉ ይልቃሉ፡፡

ሕይወት ራሱ ፍልስፍና ነው፡፡ መኖር በራሱ ጥልቅ ፍልስፍና መሆኑን ለመረዳት የራስን ተፈጥሮን ማየት በቂ ነው፡፡ የግድ ስለሠማየ ሠማያቱ ማንሳት አይጠቅብንም፡፡ ስለራስህ፣ ስለሌሎች እንዲሁም ስለዓለሙ የሚኖርህ መስተጋብራዊ ድርሻ በጎ እንዲሆን መጠነኛ ፍልስፍና ከሌለህ ራስህን ሆነህ መኖር አትችልም፡፡ ስኬታማነት ከምን አንፃር ነው ብሎ መጠየቅ በራሱ ፍልስፍና ነው፡፡ በርግጥም ፍልስፍና ከቀላል ሃሳብ ተነስቶ ወደጥልቁ ሃሳብ መስጠም ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ቀላሏን ጉዳይ አናጤናትም እንጂ በፍልስፍና ያበደች ነች፡፡ አምላክ የሠውን አዕምሮ ድንቅ አድርጎ የፈጠረው በተፈጥሮው ተደምሞ እንዲፈላሰፍና አልፎ ተርፎም የፈጣሪውን ድንቅ ጥበበኛነት እንዲያውቅ ነው፡፡

ለምሣሌ አንተ ወዳጄ ካንዲት ውብ ልጃገረድ ፍቅር ቢይዝህና ስለፍቅርህ ብለህ ከእርሷ ጋር የምታሳልፈው እያንዳንዷ ውጣ ውረድ፣ ጭቅጭቅና (ለምን ይዋሻል ፍቅር ውስጥ የከረረ ጭቅጭቅ አለ) መዋደድ በፍልስፍናዊ ሃሳቦችና በጥልቅ አስተሳሰቦች የተዋሃደና በፍቅር ቅመም የተዋበ መሆኑን ትረዳለህ፡፡ ይሄን የምታውቀው ግን ለምን እኔ እና እሷ ይሄን ያህል ተዋደድን ብለህ መጠየቅ ስትጀምር ነው፡፡ ምንዓይነት የስበት ህግ ነው እኔና እሷን ያጣበቀን ብለህ መጠየቅ የፍልስፍና ቁልፍ ነው፡፡ በርግጥ ቆንጆ ስለሆነች ወደድኳት ልትል ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ከቀላሉ ጥያቄ ተነስተህ ጥያቄህን እያዋለድከው ከሄድክ መውደድ ራሱ ምንድነው ትላለህ፡፡ አልፈህ ተርፈህ ቁንጅና ራሱ ከየት መጣ እያልክ ትፈላሰፋለህ፡፡ ማነው አንዱን ካንዱ በውበት ለያይቶ የሠራቸውም ብለህ በሃሳብህ መመንጠቅ ትችላለህ፡፡ ለምንድነው ሁሉም ቆንጆዎች የተለያዩት፤ ሁሉም ፉንጋዎችስ በፉንጋነታቸው ልዩ የሆኑት ብለህ ተፈጥሮ ላይ ልትደመም ትችላለህ፡፡

አማኝ ከሆንክ ደግሞ ይሄን ድንቅ ተፈጥሮ ውብ አድርጎና አቅለምልሞ፤ እንዲሁም ተፈጥሮ እርስበራሱ ተደጋግፎ አንዳች ሳይፋለስና ሳይጣረስ ለዘመናት እንዲኖር የፈጠረውን ፈጣሪ አብዝተህ እንድታደንቀውና እንድታከብረው ትገፋፋለህ፡፡

አይ የፈጣሪ ነገር አይመለከተኝም ካልክ ደግሞ ተፈጥሮን በራሱ ከቁሳዊነቱና ከኢነርጂው ጋር እያስተሳሰርክ የዝግመተለውጥን ልዩ መስተጋብር ታደንቃለህ፡፡ ዝግመተ ለውጡ ራሱ ከየት መጣ እያልክ ከራስህ ተነስተህ በፍልስፍና ሠማይ ጥግ መወንጨፍ ትችላለህ፡፡ በርግጥም የዳርዊን ንድፈሃሳብ ተከታይ ነኝ ካልክ የመጀመሪያው አብይ ፍንዳታ (Big bang) ከየት መጣ ብለህ መጠየቅ አለብህ፡፡ ፍንዳታው እንዴት ከምንም ተነስቶ እውን ሊሆን ይችላል ብለህ መጠየቅ ከጀመርክ አይመለከተኝም ካልከው ፈጣሪ ጋር ዞረህ ትላተማለህ፡፡ ለጥያቄህ መልስ የሚሠጥህ የተፈጥሮን ህግ አርቅቆና አወሳስቦ በሚስጥራዊ ጥበቡ እውን ያደረገው እርሱው ፈጣሪ ነውና፡፡




ወዳጄ ሠው ራሱ እኮ ቅኔ ነው፡፡ ገና ሠምና ወርቁ ያልተፈታ፡፡ ሠው ራሱ ጥልቅ ፍልስፍና ነው፡፡ ገና በወጉ ምንነቱ ያልተደረሰበትና መልስ ያልተገኘለት፡፡ የሠው ኑሮው በራሱ የፍልስፍናው መገለጫ ነው፡፡ ሠው ሃሳቡ፣ ስሜቱ፣ ተግባሩ፣ ባህርይው፣ ዋጋው፣ እጣፋንታው፣ ወዳጅነቱ፣ ጠላትነቱ፣ መልካምነቱ፣ ክፋቱ፣ ጠርጣራነቱ፣ አብሮነቱ ወዘተ ማንነቱን የሚመሠርትበት፣ ምንነቱን የሚተረጉምበት ከፍልስፍናው ሃይቅ፣ ከጥልቅ ሃሳቡ ባህር የሚጨልፈው ጥበቡ ነው፡፡ ከዚህ ጥበቡ ቀድቶም በዓለሙ ረጭቶ የሚያለመልመውና የሚያፈራው የገዛ ራሱ ፍሬው ነው፡፡

ወዳጄ አንተ ማን ነህ?? ከወዴት ነህ?? ከቶስ ምንድነህ?? ወዘተ ጥያቄዎች ገና ጥሬ እንደሆኑ ናቸው፡፡ በመልሳችን ያላበሰልናቸው ብዙ እንቦቀቅላ ጥያቄዎች በአዕምሯችን ውስጥ ይመላለሳሉ፡፡ አንተ ማን ነህ የሚለው ጥያቄ ስምን፣ ዘርን ወይም ሃይማኖትን ወዘተ የሚመለከት ሲሆን አንተ ምንድነህ የሚለው ጥያቄ ግን በጣም ጠጣርና ጥልቅ ነው፡፡ አሳብያውያን እንደሚነግሩን በዓለማችን ታሪክ ይሄን ጥያቄ የተጠየቁት ኢየሱስ ክርስቶስና ቡድሃ ናቸው ይሉናል፡፡ እስቲ ቡድሃ የተጠየቀውን አንተ ምንድነህ የሚለውን ጥያቄና የእርሱን መልስ ላንሳና ፅሁፌን ላገባደው፡፡

ቡድሃን፡- ‹‹አንተ ፈጣሪ ነህ??›› ብለው ሕዝቡ ሲጠይቁት፡- ‹‹አይደለሁም›› አላቸው፡፡ መልሠውም፡- ‹‹አንተ ከቅዱሳን አንዱ ነህ??›› በማለት ሲጠይቁት አሁንም፡- ‹‹አይደለሁም!›› አላቸው፡፡

በህዝቡ ዘንድ የቀረው ጥያቄ፡- ‹‹ታዲያ አንተ ምንድነህ??›› ነበር፡፡ ቡድሃም የሠጠው መልስ አጭርና ግልጽ ነበር፡፡ ‹‹እኔ የነቃሁ ሠው ነኝ›› በማለት መለሠላቸው፡፡ በዚህ አባባሉ ምክንያት መጠሪያው ‹‹ቡድሃ›› ተባለ፡፡ ቡድሃ ማለት በሕንድ የሳክሪት መፅሐፍ መዝገበ ቃላት ‹‹በዕውቀት የነቃ›› ማለት ነውና፡፡

ወዳጄ ፍልስፍናን በቀላል ጀምረነው በከባዱም የማንጨርሠው ነው፡፡ ነገር ግን በጠየቅን ቁጥርና መልሱን ለማግኘት በኳተንን ቁጥር በዕውቀት እየነቃን እንመጣለን፡፡ ፈረንጆቹ ከባዶ ትንሽ ነገር ይበልጣል (Something better than nothing) እንደሚሉት ካለማወቅ ማወቅ ይበልጣልና ለእውቀትና ጥበብን ለመልበስ ስንል እንፈላሠፍ እላለሁ፡፡

ፍልስፍና ጥበብን ማፍቀር ነው፡፡ ጥበብ ደግሞ ለእውነትና ለመልካምነት የቀረበች ረቂቅና የፈጣሪ መገለጫ ናት! ጥበብን ደረስንበት ማለት ፈጣሪን በሙላት አገኘነው ማለት ነው፡፡

ፍልስፍና የተፈጥሮን ቅኔነት ሠምና ወርቁን ማውጣት ነው!

ቸር ጊዜ!

_______________________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
አርብ ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.

No comments:

Post a Comment