Friday, January 26, 2018

የምንወደው ሰው በሞት ከተለየን በኋላ የመጀመሪያው በአል

የምንወደው ሰው በሞት ከተለየን በኋላ የመጀመሪያው በአል
_____________________________




የበዓል ቀን ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር አብሮ ለማሳለፍ ጥሩ ጊዜ ነው፡፡ በቅርቡ የምንወደውን ሰው አጥተን ከሆነ በዓል የሀዘን ስሜት የሚባባስበት ወቅት ሊሆን ይችላል ፡፡ ሀዘን ቀላል አይደለም በተለይ ቅርብ የሆነን ሰው ካጣን በኋላ ያለውን የመጀመሪያ በዓል ማሳለፍ አስቸጋሪና የተዘበራረቀ ስሜት ይፈጥራል፡፡ በሀዘን ውስጥ ሆነው በዓል ለሚያከብሩ የሚከተሉት ነጥቦች ደህና ሆነው እንዲያሳልፉ ይረዳሉ፡፡
 ትዝታዎችን ከቅርብ ሰዎች ጋር መጋራት፦
ያጣነው ሰው አለመኖር ካልተወራ ሀዘኑ ጠልቆ ይሰማል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእህት፣የወንድም፣የእናት ወይም የአባት ሀዘንን ላለመቀስቀስ ያረፈው ሰው ስም አይነሳም፡፡ ከዝምታ ይልቅ ያሳለፏቸውን የበዓልም ሆነ ሌሎች ትዝታዎች መጋራቱ ይረዳል፡፡ የሚያስቁ ገጠመኞችን፤ ያደርጉ የነበረውን ነገሮች መነጋገሩ ሙሉ ለሙሉ ኖርማልና እርም ለማውጣት የሚያግዙ ነገሮች ናቸው፡፡በተጨማሪም የሚሰማንን ስሜት መግለፅ፣ አብረን ያሳለፍናቸውን ጥሩ ጊዜያት ማስታወስ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ከፍተኛ የሆነ ተስፋ መቁረጥና ብቸኝነት ወደ ራስን መጉዳትና አብዝቶ አልኮል መጠቀም እንዳያስከትል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የሚሰማንን ስሜት ከሚጋሩ ሰዎች ጋር አብሮ ማሳለፍ የብቸኝነት ስሜትን ይከላከላል፡፡
•የበዓል ግዴታዎችን መቀነስ፦
በዓላት ሲመጡ ግዴታዎች ተከትለዋቸው ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ዘመድ መጠየቅ፣ስጦታ መስጠት፣የመስሪያ ቤት ዝግጅቶች የመሳሰሉት፡፡ ተያይዞ የሚመጣውን ጫና ለመቀነስ ለራስ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ተገልሎ ብቸኛ መሆን ሳይሆን ጫና የሚፈጥሩ ግዴታዎችን መቀነስ ጥሩ ነው፡፡ ዝግጅቶች ላይ መሳተፍ ባንፈልግ ሰዎች በሀዘኑ ምክንያት እንደሆነ ይረዱናል፡፡ ቀለል ያሉ፣ የማይመች ስሜት የማያስከትሉና ጫና የማያመጡ ዝግጅቶች ላይ መሳተፍ ጥሩ ነው፡፡
•በአልን በአዲስ መልኩ ማክበር
ሀዘን ላይ ስንሆን በአል የማክበር ስሜት ላይኖረን ይችላል፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ሀዘን ከበአል የምንወደውንና ብዙም ያልሆንበትን ነገር ለመለየት እድል ይሠጠናል፡፡ ከተለየን ሰው ጋር በተለየ መልኩ በበአል አብረን እናደርግ የነበሩ ነገሮችን በማድረግ በልባችን ያለውን ትልቅ ቦታ ማክበር ይቻላል፡፡
የምንወደውን ሰው ካጣን በኋላ ያለው የመጀመሪያው በዓል ከባድ ነው፡፡ያጣነውን ሰው ምንም ነገር ሊተካው አይችልም፡፡ ነገር ግን ራስን ሳይጎዱ ያጣነውን ሰው በማስታወስ ማሳለፍ የሚሰማንን ሀዘንና ጉዳትን ይቀንሰዋል፡፡
መልካም በዓል፡፡
የአዕምሮ ጤና
ምስል- ከድረ-ገጽ

No comments:

Post a Comment