Friday, January 26, 2018

“ይቅርታ ተባሉ፣ አልተባሉ ምን እንዳያመጡ ነው” (ኤፍሬም እንዳለ)

“ይቅርታ ተባሉ፣ አልተባሉ ምን እንዳያመጡ ነው” (ኤፍሬም እንዳለ)



በዛ ሰሞን ከአንዳንድ አቅጣጫዎች “ይቅርታ” የሚመስሉ ቃላቶች ሰማን ልበል! ዘንድሮ ነገሮች ሁሉ በቃላት ድሪቶና “እንዲህ የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው…” በሚሉ የተለመዱ መቀነቶች ስለመዋጡ ምን እንደተባለና ምን እንዳልተባለ ማወቁም ግራ የሚያጋባ ሆኗል፡፡
ዳኛው ተከሳሹን…
“ለፈጸምከው ወንጀል ይቅርታ ከጠየቅህ በግሳጼ ትለቀቃለህ፣” ይሉታል፡፡
“ጌታዬ፣ ምን ብዬ ነው ይቅርታ የምጠይቀው?”
“ህብረተሰቡ ላይ ላደረስኩት ችግር ይቅርታ እጠይቃለሁ በላ!”
“ጌታዬ አኔ መች ችግር አደረስኩ?”
“ህገ ወጥ አልኮል ስታመርት ተይዘሀል፣ አይደል እንዴ!”
“እኔ፣ ጌታዬ! በጭራሽ እንደዛ አላደረግሁም፡፡”
“በጭራሽ ማለት ምን ማለት ነው! አልኮል ማምረት የሚያስችሉ መሳሪያዎች አሉህ አይደለም እንዴ?”
“እንደዛ ከሆነ ጌታዬ በአስገድዶ መድፈርም ይክሰሱኝ፡፡
“ለምን? የሆነች ሴት አስገድደህ ደፍረሀል እንዴ?”
“ጌታዬ አልደፈርኩም…ግን እንደዛ ማድረግ የሚያስችል መሳሪያው አለኝ፣” አለና አረፈው፡፡
በእርግጥ ይሄ ለፍርድ ያስቸግራል፡፡
ዘንድሮ እኛ ዘንድ ይቅርታ ሊጠየቅባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ብዙ ጥፋቶች አሉ…ሆነ ተብለው ከቅንነት ጉድለት የሚፈጸሙ፣ በስልጣን ወይም በሀብት ሽፋን በማን አለብኝነት የሚፈጸሙ፣ ሳናውቅ የምናውቅ እየመሰለን በእውቀት ማነስ የሚፈጸሙ፣ “ሰለሰው፣ ስለሰው ቀድጄ ልልበሰው” በሚል አይነት አመለካከት በግዴለሽነት የሚፈጽሙ፡፡ ምነዋ ታዲያ ይቅርታ ጠያቂዎች አነስን!
በነገራችን ላይ… ይቅርታ ጥሩ ነገር ነው፡፡ የተበላሸውን ባይጠግንም ቢያንስ፣ ቢያንስ ጥፋትን አምኖ ይቅርታ ማለት መሸነፍ ሳይሆን ማሸነፍ ነው፡፡ ዝቅ ማለት ሳይሆን፣ ከፍ ማለት ነው፡፡ የመንፈስ ድክመትን ሳይሆን የመንፈስ ጥንካሬን የሚያሳይ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን በግለሰብም፣ በቡድንም ሆነ በድርጅት ደረጃ ይቅርታ መጠየቅ በራስ ላይ እድሜ ይፍታህ መፍረድ የሚመስላችው በዝተዋል፡፡
“ይቅርታ ተባሉ፣ አልተባሉ ምን እንዳያመጡ ነው” አይነት አመለካከት የብስለት ምልክት አይደለም፡፡
የሆነ ዓመት በዓል ይመጣል፡፡ የመብራት ሰዎች በበዓሉ ሰሞን የመብራት መቆራረጥ እንዳይኖር ዝግጅት ተድርጓል ይሉናል፡፡ እንደውም ከፍትኛ ሀይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች እንዲተባበሩ ይደረጋል ምናምን ይባላል፡፡ “ጎሽ…እሰየው ነው፡፡ እውነት በዓልን ሳናማርር፣ ደስ ብሎን በሰላም ልናሳልፍ ነው!” እንላለን፡፡
መልሳችንን በፍጥነት ነው የምናገኘው፡፡ ገና የዋዜማዋ ፀሀይ ብልጭ ስትል እዚህ ሰፈር ድርግም፡፡ ረፈድ ሲል እዛኛው ሰፈር ድርግም፣ ሲል ውሎ ያድራል፡፡ በበዓሉ ቀን እየተደዋወልን እንኳን አደረሰህ/አደረሰሽ ከመባባል ይልቅ ዋናው ጥያቄያችን “እናንተ ሰፈር መብራት አለ?” ይሆናል፡፡
በዓል ያልፋል፡፡ ሁሉም ጭጭ! ያሳሳቱንስ! በቤታችን በማብስያ እጦት ለተበላሹብን ነገሮችስ! ለማያደርጉት ነገር በአጉል ተስፋ ስሜታችንን አበላሽተው በዓላችንን የነጠቁንስ! “ከአቅም በላይ በሆነ ችግር…” ወይም ሌላ ነገር ብሎ ይቅርታ መጠየቅ ማንን ገደለ! ቢያንስ፣ ቢያንስ ይቅርታ አንጠየቅም እንዴ! “ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት…” አይነት ነገር ተብሎ ህብረተሰቡን ይቅርታ አይጠየቅም እንዴ፡፡ የተበላሸውን በዓል መልሶ አያመጣም ይሆናል -ቢያንስ ቢያንስ ግን ክብር መስጠት ነው፡፡
ይኸው ብዙ የአዲስ አበባ መንገዶች የእግረኛ አበሳ ሆነው ከርመዋል፡፡ ለሳምንታት በአቧራና ወፍራም የጫማ ሶል አልፎ በሚያም መንገድ ላይ ስንንከላወስ ከርመናል፡፡ መጠገኑ ጥሩ…ይሄን ያህል ጊዜ መቸገር ይገባን ነበር እንዴ! ቢያንስ፣ ቢያንስ ይቅርታ መጠየቅ ማንን ገደለ! የማንን ኮከብ ከትከሻው ላይ አወረደ!
ኮንዶሚንየምና አንዳንድ ሪል ስቴተ አፓርተመንቶች ውስጥ አየኖሩ ለረጅም ጊዜ መብራት የሌላቸው ብዙ ወገኖች ናቸው፡፡ ወሀ መጣች፣ አልመጣች እያሉ ተቀምጠው የሚያድሩ ብዙ ናቸው፡፡ እነኚሀ አገልግሎቶች የማሟላት ነገር የሚመለከታቸው ሰዎች ደግነት፣ መልአክነት ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ መብራት ያላገኙት፣ ውሀ ያላገኙት ሀላፊነታቸውን ያልተወጡ ክፍሎች ስላሉ ነው፡፡
ወንበር ከማሞቅ የዘለለ ተግባር የማይፈጽሙ ሰዎች ስላሉ ነው፡፡ በየወሩ እዳቸውን አየገፈገፉ፣ አንዳንዶቹም መኖሪያ አገኘን ብለው አጠናቀው ከፍለው… ጄሪካን ተሸክመው ውሀ ፍለጋ መንደር ለመንደር መዞር አላበቸው እንዴ! የሚመለከታቸው ሰዎች ቢያንስ፣ ቢያንስ ይቅርታ ቢጠየቁ ምናቸው ይነካል! ‘ተገልጋይን ይቅርታ መጠየቅ የመጀመሪያ ደረጃ የዲሰፕሊን ጉድለት ነው፣’ የሚል አንቀጽ የቅጥር ውላቸው ላይ ሰፍሯል እንዴ!
“ይቅርታ ተባሉ፣ አልተባሉ ምን እንዳያመጡ ነው” አይነት አመለካከት የብስለት ምልክት አይደለም፡፡
የኮንዶሚኒየም እዳቸውን ሲከፍሉ ይከርሙና ድንገት የ“ጨምሩ” መልእክት ይመጣል፡፡ እየከፈሉ ያሉት ላይ ማስተካከያ አይነት በሚል፣ ወደኋላ ሄዶ “ይሄን ያህል ጨምር፣ ይሄን ያሀል ጨምሪ፣” ይባላል፡፡ ዝም ብሎ “ጨምሩ” ማለት እንዲሀ ቀላል ነው እንዴ! ሀምሳ ብርም ትሁን መቶ ብር ሰዉ እኮ ከጉሮሮው ነጠቃ ነው እኮ የሚሆንበት!
ከልጆቹ ጉሮሮ ነጠቃ ነው እኮ የሚሆንበት! ለባለቤቱ መድሀኒት መግዣ ካስቀመጠው ነጠቃ ነው እኮ የሚሆንበት! እንኳን ጨምሩ ተብሎ እንዲሁም ሕይወት የመሰንበት ነገር ብቻ ሆናለች፡፡ ግን ጭማሪውን ባያስቀረውም “ይሄ በመፈጠሩ ይቅርታ እንጠይቃለን፣” ማንን ገደለ! ይቅርታ በማለቱ የመንግሥተ ሰማያት ይለፍ የተሰረዝበታል እንዴ!
ይኸው የግል ትምህርት ቤቶች እንደፈለጉ፣ ባሰኛቸው ሰዓት ዋጋ ይጨምራሉ…ይጨምራሉ ብቻ ሳይሆን ይከምሩታል፡፡ አብዛኛው ወላጅ እኮ ልጁን ሲያስመዘግብ የትምህርት ቤት ክፍያውን በጀት አድርጎ፣ ከየትም ቀንሶ፣ ከየትም ተበድሮ እንደሚያቻችለው ወስኖ ነው፡፡ ግን ወላጅ የተባለውን ጭማሪ ሳይወድ በግዱ ይከፈላል…ከልጁ ትምህርት የሚበልጥበት ነገር የለምና፡፡ እንዲህም ሆኖ “ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ እንጠይቃለን” ማለት የማንን ካዝና ገለበጠ!
ስብሰባ ይጠራል፣ ‘አስቸኳይ’ ምናምን ይባላል፡፡ በእለቱ ተሰብሳቢው ወደተባለው ስፍራ ሲሄድ በሩ ላይ ስበሰባው ለተከታዩ ሳምንት መተላለፉን የሚገልጽ ማስታወቂያ ተለጥፎ ይጠብቀዋል፡፡ እንዲሁ በቀላሉ ብጣሽ ወረቀት ለጥፎ ‘አለቀ፣ ደቀቀ’ ብሎ ነገር አለ እንዴ! የሰዉስ ልፋት! ለስብሰባው ሲል ያበላሻቸው ፕሮግራሞቹስ! ያጠፋው ጊዜና ገንዘብስ! ቢያንስ፣ ቢያንስ “ከአቅም በላይ በሆነ ችግር…” አይነት ሰበብ ሰጥቶ ይቅርታ ማለት ማንን ገደለ!
“ይቅርታ ተባሉ፣ አልተባሉ ምን እንዳያመጡ ነው” አይነት አመለካከት የብስለት ምልክት አይደለም፡፡
በሆነ ባልሆነው “በአምስት ዓመት ከአፍሪካ ቀዳሚ፣ ከአፍሪካ ተመራጭ፣ ከአፍሪካ ቁንጮ እናደርገዋለን” አይነት ነገር እያሉ የተንኮለኛው ከበደ ታሪክ የሚተረክልን አራሶች የምንመስላቸው ሁሉ ለድፍረታቸው ሁሉ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባል፡፡ በነገራችን ላይ… አፍሪካ ማለት ምን ይምስላቸዋል?
አንዳንድ ጊዜ ግራ ይገባናል፡፡ ምናልባት ሰዎቹ ያዩት ካርታ የተሳሳተ ይሆን ይሆናል፡፡ ምናልባት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ማለት ሱዳን፣ ጅቡቲና ሶማሊያ ብቻ ይመስሏቸው ይሆናል – ዘንድሮ በገጠመን ከፍተኛ ደረጃ የእውቀት ድርቅ ይህ አይሆንም አይባልምና!
እነሱ ገንዘብ በአካፋ ስለሚዝቁ ብቻ በየስፍራው አምስተኛ ዜጋ አይነት ሰሜት እንዲሰማን ሊያደርጉ የሚሞክሩ ሁሉ ለድፍረታቸው ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባል፡፡ ዘንድሮ ባለገንዘብ ከመሆን ጋር አብሮት የሚመጣው ማን አለብኝነት በዝቷልና! እንኳን በእነሱ አጠገብ አልፈን… መኪናቸውን እንኳን ስንነካ ሊጠየፉ የሚዳዳቸው የፋስት መኒ ባለገንዘቦች በዝተዋልና!
በእነሱ ድክመት፣ በእነሱ ምክንያት ለተፈጠረው ነገር ሁሉ እኛን ተጠያቂ ሊያደርጉን የሚፈልጉ፣ እነሱ ወንበራቸውን ለመጠበቅ እኛን የአብረሀም በግ ሊያደርጉን የሚፈልጉ፣ ለዚህ ዘመን ችግር የጥፋተኝነቱን ጦር አስርት ዓመታት ወደኋላ የሚወረውሩ ሁሉ ለድፍረታቸው ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባል፡፡ ዘንድሮ ብትንሹም፣ በትልቁም አመልካች ጣትን ወደሌላ መቀሰር ልምድ ሆኗልና፡፡
“ይቅርታ ተባሉ፣ አልተባሉ ምን እንዳያመጡ ነው” አይነት አመለካከት የብስለት ምልክት አይደለም፡፡
ፖለቲካ ሳያውቁ ወንበር ስለያዙ፣ እንትን አገር ሄደው ንግግር ስላደረጉ፣ በቴሌቪዥን የአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የአየር ሰዓት ስለተሻሙ ብቻ በባዶ ሜዳ ትከሻቸውን የሚያሰፉብን ለድፍረታቸው ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባል፡፡ ህዝብን ከመድፈር የከፋ ጥፋት፣ ህዝብን ከመድፈር የከፋ ሀጢአት የለምና!
እግረ መንገድ ግን ከልባችን ሳይሆን ቅንነት በጎደለው መንገድ ይቅርታን የምንጠቀምበት አለን፡፡
“ጸንሻለሁ፡፡”
“ምን?”
“ጸንሻለሁ!…አይሰማህም እንዴ!”
“እንዴት ተፈጠረ?”
“እንዴት ተፈጠረ! እንዴት ተፈጠረ ትለኛለህ? ጥንቃቄ እናድርግ ስልህ አንተ አይደለህም ያለጥንቃቄ… ፡፡”
“እሺ፣ እሺ…አሁን ትዝ አለኝ…በቃ ይቅርታ፣ ተጸጽቻለሁ፡፡”
እንዴት ነው ነገሩ… ልጅን ያህል ነገር እኮ ነው የተሸከመችው! የእሱ ተጸጽቻለሁ…የዘጠኝ ወር ስቃዩን ይቀንሰዋል? በሰው ሕይወት ቀልዶ ተጸጽቻለሁ ብሎ ነገር አለ እንዴ! “በቃ ይቅርታ፣ ተጸጽቻለሁ” ብል የሚቆም ነገር ነው እንዴ!
ፖለቲከኞች… “አዎ ከፓርቲው መስመር ወጥቼ ነበረ..አሁን ተጸጽቻለሁ፣” ምናምን ይላል፡፡
ከመስመር ከወጣ እኮ በቃ ያኛውን መስመር ትቶታል ማለት ነው፡፡ ለጠቅላላ እውቀት ያህል… መፈንቅለ መንግሥት ምናምን እንደሚባለው መፈንቅለ ፓርቲ ምናምን የሚባል ነገር አለ እንዴ! “እኔ ነኝ መሪው፣” “የለም እኔ ነኝ መሪው” እየሉ የሚተናነቁት ነገር እኮ ግራ እያጋባን ነው! በወር ሀምሳ ብር የሚጣልበት እቁብ እንኳን ስርአት አለው! እንላለን፡፡ በእኛ ስም ለሚፈጥሯቸው ችግሮች ሁሉም ወገኖች ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባል፡፡
እና…ሁላችንንም የአራስ ልጅ ጭንቅላት ያለን ማስመሰል ጥፋት፣ የጥፋት ጥፋት ነው፡፡
እዛ ላይ ቁጭ ያሉ ሰዎች ይቅርታ መጠየቅ ለደረጃቸው የማይመጥን ይመስላቸዋል፡፡ እንደፈለጉ ተናግረውን፣ እንደፈለጉ ከፍ ዝቅ አድርገውን… እንደፈለጉ ቀሺም ቡድን እንደሚያንገላታት ኳስ አድርገውን ሳለ እንኳን ይቅርታ ሊጠይቁን ከእነመኖራችንም ይረሱናል፡፡ ጥያቄ አለን…እነኚህ ከእኛ ከፍ ብለው ከተቀመጡት ሰዎች ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉት አቆልቁለው ሲያዩን እናንስባቸዋለን እንዴ!
ጥሬ ነገር እናክልባቸዋለን እንዴ! ሰው እንሁን አሻንጉሊት ለመለየት እናስቸግራቸዋለን እንዴ! ለዚሀ ነው እንዴ እነሱ ላይ ሆነው፣ እኛ ታች ያለነውን ይቅርታ ማለት የማይዋጥላቸው!
በነገራችን ላይ…ግን እኮ ትልቁን ወንበር የተሸከምነው እታች ያለነው ነን እኮ፡፡ ፈርሶ ተመልካች ያጣ መንደር የመሰለው እኮ የእነሱን ወንበር የተሸከመው የእኛ ትከሻ ነው፡፡ ግን እንዴት ብለው ይቅርታ ይጠይቁን! የኛ ትከሻ ሲበቃውና ዘወር ስንል እኮ ከዛ በኋላ ወንበሩ ማረፊያ ስፍራ የለውም፡፡ ይሄንን ለማወቅ እኮ የአይንስታይንን አእምሮ መመኘት አያስፈልገንም፡፡
“ይቅርታ ተባሉ፣ አልተባሉ ምን እንዳያመጡ ነው” አይነት አመለካከት የብስለት ምልክት አይደለም፡፡

No comments:

Post a Comment