Thursday, February 1, 2018

‹‹የምፅፈው ሕይወትን ሁለቴ ለማጣጣም ነው፡፡ አንድም ባለፈው ሕይወቴ፤ አንድም ባሁኑ ሕይወቴ፡፡››

(
...)


ወዳጆች ማርክ ትዌይን ‹‹የምታውቀውን ሁሉ ፃፍ›› ይላል፡፡ ሠው ባይፅፍ ኖሮ የዓለማችን ስልጣኔ ምን እንደሚሆን አስቡት፡፡ ጥበባዊ ስራዎች በፅሁፍ መገለፅ ባይችሉ ኖሮ ውስን ይሆኑ ነበር፡፡ ዛሬ እያነበብን ቀልባችን የምንሠበስብባቸው፣ አደብ የምንገዛባቸው፣ የምንዝናናባቸው፣ ነፍስያችንን የምናጠግባቸው፤ ብቸኝነታችንን የምንሸሸግባቸው፤ እንደአማካሪ ሆነው ሃሳብ የምናገኝባቸው፤ ህገ ደንብ ሆነው የምንመራባቸው፤ ውስጣዊ ቃጠሎአችንን የምናስታግስባቸው፣ በእውቀት የምንበስልባቸው፤ ወዘተ.. በስሜት ከፍ ዝቅ፣ እላይ ታች እንድንናጥ የሚያደርጉን ፅሁፋዊ ስራዎች ናቸው፡፡ ባንጽፍ ኖሮ እዚህ ስልጣኔ ላይ ለመድረስ ሌላ ብዙ ዓመት ወደኋላ ይመልሰን ነበር፡ የዕውቀት ሽግግሩ ቃላዊ ስለሚሆን ውጤታማ መሆን አይቻልም ነበር፡፡ አባቶቻችን በቃል ያለ ይረሳል፤ በፅሁፍ ያለ ግን ይወረሳል እንዲሉ፡፡

ታዲያ ለምንድነው እኔ የምፅፈው ብዬ ራሴን ስጠይቅና አንድ ሠው ለምንድነው የምትፅፉት ብሎ በዚሁ ግሩፕ ሲጠይቅ ጥያቄው እኔንም ስለሚመለከት እንዲህ አልኩ፡-…


እኔ የምፅፈው እኔ የደረስኩበትን እውነት፣ እውቀትና እምነት ለብዙሃኑ ለማካፈል ነው፡፡ የምጽፈው በውስጤ ልውጣ አልውጣ እያለ የሚተናነቀኝን የሃሳብ ፍንዳታን ለማስታገስ ነው፡፡ የምፅፈው ሌሎች ስለማያውቁ ነው ብዬ ሳይሆን የእኔ ሃሳብ በዚህ ጉዳይ ላይ ይሄ ነው እያልኩ ነው፡፡ የምፅፈው ሃሳብን መግለፅ ተፈጥሯዊ ፀጋዬ ስለሆነ ነው፡፡

የምፅፈው ለራሴና ለሌሎች ለመጮህ ሊሆንም ይችላል፡፡ የምፅፈው እኔ ያልኩት ብቻ እውነት ነው ለማለት ሳይሆን በእኔ በኩል የሚታየኝ እውነት ይሄ ነው ለማለት ነው፡፡ የምጽፈው ያወቅኩትን ነገር ለሌሎች አሳውቅ ዘንድ ተፈጥሯዊ ውስጣዊ ግፊት ስለሚንጠኝ ነው፡፡ የምፅፈው የእኔ ሃሳብ ከሌሎች ጋር በመፃመር አዲስ ሃሳብ መስራት ይችላል ብዬ ስለማምን ነው፡፡ የምፅፈው የውስጤ እሪታ ምን ያህል እንደሚበጠብጠኝ ለውጪው ዓለም እወቁልኝ ለማለት ነው፡፡ የምጽፈው ተናግሬ እፎይ ለማለት ነው፡፡
የምፅፈው ተንፍሼ ለመገላገል ነው፡፡ የምፅፈው ልክ ባልና ወንድሟ በአፄ ቴዎድሮስ እንደተገደሉባት ሙሾ አውራጅ (ምንትዋብ) እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ለማደር ነው፡፡ የምፅፈው በፍጥረተዓለሙ ተደምሜ አድናቆቴን ለጥበበኛው ፈጣሪ ለመግለፅ ነው፡፡ የምፅፈው የተፈጥሮን ቅኔነት በአቅሜ ፈትቼ ሠምና ወርቁን ይሄ ነው ለማለት ነው፡፡

ወዳጆች በምፅፈው ሃሳብ ገንዘብ ባገኝበት ክፋት የለውም፡፡ ይሄ በራሱ ችግር የለውም፡፡ ችግሩ የምፅፈው ነገር ገንዘብ ተኮር ሆኖ ይዘቱ መገንዘብ ከጎደለውና ከገለባ ከቀለለ ብቻ ነው፡፡ መገንዘብ ከገንዘብ ይበልጣልና፡፡ የምኖረው ለመፃፍ ከሆነም ደግ ነው፡፡ በመፃፍ መኖር ፍስሃ ነውና፡፡


በነፃነት ሃሳብን ማስፈር ራስን መሆን ነው፡፡ የውስጥን መተንፈስ ከውስጣዊ ግብግብ እረፍት ማግኘት ነው፡፡ በመፃፍ ውስጥ ማስታወስ አለ፡፡ በማስታወስ ውስጥ ማመላለስ አለ፡፡ በማመላለስ ውስጥ ማብሠልሠል አለ፡፡ በማብሠልሠል ውስጥ አዲስ ሃሳብ መጨመር አለ፡፡ አዲስ ሃሳብ በመጨመር ውስጥ አዲስ እውቀት አለ፡፡ በአዲስ እውቀት ውስጥ አዲስ ሠው*ነት አለ፡፡ አዲስ ሠው*ነት ደግሞ አዲስ ማንነት ነው፡፡ አዲስ ማንነት ደግሞ አዲስ ደስታ ነው፡፡ አዲስ ደስታ ደግሞ የመኖራችን ምክንያት ነው፡፡
‹‹የምፅፈው ሕይወትን ሁለቴ ለማጣጣም ነው፡፡ አንድም ባለፈው ሕይወቴ፤ አንድም ባሁኑ ሕይወቴ፡፡››
እናንተስ ለምንድነው የምትፅፉት?? የማትፅፉትስ ብትሆኑ ለምንድነው የማትጽፉት??


ቸር ጊዜ!
______________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (...)
ሐሙስ ጥር ፳፬ ቀን ፳፻፲ ..


No comments:

Post a Comment