Saturday, February 10, 2018

የአድዋ ተራሮች

የካቲት 23 ቀን 1888 . ለኢትዮጵያዊያን  የጭንቅና የደስታ ቀን ነበር። ማለትም ከዛሬ 122 ዓመታት በፊት።  ዕለቱ ሰንበት ነው። እናም በዚህ ጊዜ ወደ ውጊያ መውጣት ባይታሰብም ክብሩ የተነካው አርበኛ ህዝብ ግን ዓድዋ ላይ ቀፎው እንደተነካበት ንብ እዝ ብሎ ወጣ። ተንቀሳቅሶም ውጊያን ከእብሪተኛውና ዘመናዊ መሣሪያን ታጥቆ ከሚጠብቀው የጣሊያን ጦር ጋር አደረገ። ከማለዳ አንስቶ ጀንበር እስክታዘቀዝቅ ባለው ጊዜም ትንቅንቁን አጧጧፈው።  የተካሄደው ጦርነት እልፍ አእላፍ ሰዎችን መስዋዕት የጠየቀ ቢሆንም ድሉ ግን ከኢትዮጵያዊያን እጅ  አልወጣም።
ጣሊያንንም ከአምባላጌ እስከ ዓድዋ ተጠራርጎ ማባረር ችሏል። «የጥቁሮች ድል!» በሚልም ዓለም ያወደሰውን ተግባር ተፈጽሟል። የጣሊያን መንግሥት የሐፍረት ማቅን በግዱ እንዲከናነብም አድርጎታል። ድሉ ከመጣ በኋላም ቢሆን እንዲሁ የወረራው መነሻ የሆነውን የውጫሌ ውል እንዲፈርስ አድርጎ የጣልያን መንግሥት በውጫሌ ውል የነበረውን አጉል ምኞት እንዲከሽፍ አስችሏል።

ወራሪው በሽንፈቱ አፍሮ የኢትዮጵያን ሙሉ ነፃነት አውቆ እና ተቀብሎ የሰላም ስምምነትም እንዲፈርምም  ሆኗል። ይህ ስምምነት በእርግጥ ለነጮች እንግዳ ነገር ነበር። ምክንያቱም ጥቁሮች አያሸንፉንም ብለው ስለሚያምኑ። ይሁንና ከጥቁሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ግን ይህንን አሳይታለች። የተረጋገጠ ሉአላዊ መንግሥት እንዳላትም በውድም ሆነ በግድ ተቀብለው እንዲያረጋግጡ አድርጋለች። ታዲያ ከዚህ የበለጠ ድል ከየት ይገኛልይህንን መነሻ በማድረግም ትውልዱ ልክ የዛሬ 121 ዓመት እንደተከሰተው የድል በዓሉን ለመዘከር ሽር ጉድ ማለቱን ተያይዞታል።

ታላቁ የዓድዋ ድል በዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ እንደተበሰረ ሁሉ ወጣቶችም ዛሬ ላይ መነሻቸውን አዲስ አበባ አድርገው ተራራውን፣ ኮረብታውን በእግራቸው እያቆራረጡ የካቲት 23ዓደዋ ላይ ያርፉና ክብረ በዓሉን ያደምቁታል። አርበኞች አባቶችም ቢሆኑ በዚሁ በቅርባችን በአዲስ አበባ እንኳን በአርበኝነት ልብሳቸው ከመቼውም በላይ አምረውና ደምቀው ይታያሉ። ይሸልላሉ፣ ቅኔውን ይዘርፋሉ፣ ዜማና ግጥሙንም ያንቆረቁሩታል። ስለዚህም ለዚያ የሚሆናቸውን ስንቅ እየሰነቁ ናቸው።

በእርግጥ ይህ የጥቁር ህዝቦች የድል በዓል ከዚህ በላይ በየጊዜው ሊነሳና ሊወደስ የሚገባው ነው። በቅኝ ግዛት አንያዝም ብለው የዓድዋ ድል እውን እንዲሆን አቀበት የወጡ፣ ቁልቁለት የወረዱ ፣እርጥብ የጨሰባቸው፣ደረቅ የነደደባቸው፣ ከቤታቸው የተፈናቀሉ፣ የቆሰሉ፣ የሞቱ ጀግኖቻችን አልፋና ኦሜጋ የማይረሳ ትዝታ አላቸውና። ሆኖም ሰው ባለው አቅሙ ነውና ምስጋናን የሚቸረው ሁሉም አቅሙ በፈቀደ ዘላለም ያወድሳቸዋል። ከህሌናውም አያጠፋቸውም። ስለሆነም ማን ምን እያለ አወደሳቸው ቢባል መልስ የለውም። ምክንያቱም ብዙዎች ስለእነርሱ ተናግረዋልና፤ ብዙዎችም አዚመዋል፤ ብዙዎችም በብዕራቸው ተጠበውላቸዋልና ነው።  እንኳንስ የታሪኩ ባለቤቶች ኢትዮጵያውያን የዓለም ህዝብ ስለ ዓድዋ ብዙ ነገር ተናግሮለታል።

በመጀመሪያ የዓድዋ ድል እንዴት መጣ ወደሚለው ጉዳይ እንሸጋገር። ይህ ድል የመጣው በብዙኃኑ ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ እንደሆነ ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ታዲያ እኛም የኪነጥበብ ሰዎች ተሳትፎ ምን ነበር የሚለውን ብቻ እንዳስ።

በዓድዋ ታሪክ የጦር መሳሪያ አንግበው ቦምብ ካፈነዱት ምላጭ ከሳቡት ጀግኖች ውጪ  ለጀግኖች ሞራል የሚሰጡ ኢትዮጵያውያን እንዲህ በቀላሉ የሚጠቀሱም አይደሉም። ጸሐፊዎች እና ባለቅኔዎች እንዲሁ ገጣሚዎች ብዙ ብለዋል። ይሁንና አንዳንዶቹ ግጥሞች በአዝማሪዎች፣ በእረኞችና ባልታወቁ ግለሰቦች የተነገሩ ስለሆኑ እገሌ አላቸው ማለት ይከብዳል። ሆኖም ግን ከመዘወተራቸው የተነሳ የህዝብ ግጥም እየሆኑ ስለመጡ እኛም ያለ ጠቋሚ ማስቀመጥ እንችላለን። በእርግጥ በዚች አምድ ብቻ በዓድዋ ላይ የተገለጹ፣ የተነገሩና የተዜሙ ነገሮችን ማንሳት ከባድ ነው። ይሁንና ከብዙ በጥቂቱ እንካችሁ ተመገቡ ለማለት ወደድን።


ከድምፃዊያን አንደበት
አንጋፋው ድምፃዊ ተሾመ አሰግድ «እንደው ዘራፌዋ» በሚለው ዜማው እንዲህ ነበር  ያለው፤
 «...መቅደላ አፋፉ ላይ ጎበዝ ወንድ ሆነበት
በመተማም ጎራ ጀግኖች አንድ ሆኑበት
እንዳይሞት ሆነ እንጂ  ስሙን እንዳይቀብሩት
የመቅደላን መንደር የዶጋሊን ሜዳ
የማይጨው ዓድዋን የመተማን ሜዳ
ተዳኘበት እንጂ መች ዋኘበት ባዳ
አፄ ቴዎድሮስ አባ ታጠቅ ካሳ
እምዬ ምኒልክ ጥራኝ የእኔ አንበሳ
በደም ታዋጋለህ  በአካል ባትነሳ ... በማለት የእነርሱን ታላቅነት ምን ያህል እንደነበር አዚሞታል። ቀጠልም አድርጎ እንዲህ ነበር ያለው።
ሙት ፈራሽ ተብሎ ሲተረክ ሲወራ
ሟች አፈር ተብሎ ሲነገር ሲወራ
ባልቻ ተወለደ  ዳግም ፍሬ አፈራ
የትውልድን ታሪክ ትውልዱ ካደሰው
የአባቱን ጎራዴ ብታንቀሳቅሰው
ዮሐንስ አሉላ ሥራዬን አይወቅሰው
ዘራፍ ዘራፍ ሲል ነው የጀግና እውነቱ
ጎራው ጎራው ሲል ነው የጀግና ድፍረቱ
ማን ተኝቶ ያድራል ሲነካ መሬቱ...» በማለትም መሬቱ እንዳይነካ ምን ያህል እንደተፋለሙ ያስቀምጠዋል።


ሌላው ሙዚቀኛ ውብሸት ፍስሐ በበኩሉ «እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያን አገራችንን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ከድንበር መልሱ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ድንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤  ጠላት በመጣበት በኩል ሁላችሁም ሄዳችሁ በአንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ። እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ» በማለት የሚመክሩትን አርበኞች እንዲህ ሲል አወድሷቸዋል።
የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ
ዘራፍ ዘራፍ ማለት ሁልጊዜ እሻለሁ
ከእናት ከአባት አገር ትውልድ ወርሻለሁ
እምም ነው ጭልጥ ነው ውሃ አይላመጥም
ጠላት ወዳጅ ላይሆን አልለማመጥም 
...

ሥጋዬንም እንኩ አጥንቴንም እንኩ
ነገር ግን አገሬን በምንም አትንኩ  ... በማለት ያወድሳቸዋል፡፡
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደም እና ከአጥንት
ዓድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት
መቼ ተረሱና የወዳደቁት። እያለች እጅጋየሁ ሽባባው አዚማዋለች።


ከጸሐፍት ጎራ 
ከድምፃዊያኑ ጎራ ወጥተን ደግሞ ወደ ፀሐፍቱ ስንመጣ እንዲህ በማለት ይገልጿቸዋል። 1888 . ኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ሕልሟን እውን ለማድረግ በተነሳች ጊዜ ሰበበ ጦርነት የሆነው የውጫሌው ውል ነበር፡፡ በአንቀጽ 17 በኢጣሊያንኛ ትርጉሙ «ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ጥብቅ ግዛት ነች፤ የውጭ ግንኙነቷ በርሷ በኩል ይሆናል» የሚለው የተጭበረበረ ሐረግ ነበር ፍልሚያ ውስጥ የከተታቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንም የውስጥ ችግራቸውን ወደጎን ትተው ከየማዕዘኑ ተጠራርተው በአፄ ምኒልክ መሪነት ከፍልሚያው አውድማ ተሰለፉ፡፡ እናም የኪነት ባለሙያዎች በሥነ ቃል፣ በሥነ ግጥም፣ በቅኔ ወዘተ...ስለ ጦርነቱ ብዙ ብለዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን አንዱ ናቸው።
ጸጋዬ  «! . . . ያቺ ዓድዋ» «እሳት ወይ አበባ» ከተሰኘው የሥነ ግጥም መድብላቸው ስለ ዓድዋ እንዲህ ብለዋል።
. . . . !
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ሥርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ለት፤ . . .
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኘው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው በለው ሲለው
በለው - በለው - በለው!
! . . . ዓድዋ . . .


አዝማሪዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት ይሰጡት የነበረው ወኔ ቀስቃሽ ዝማሬ ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ያስቀመጡት ደግሞ ቤርክሌይ የሚባሉት ጸሐፍት ናቸው። እኒህ ፀሐፊ ከጉዞው ጋር አያይዞ ነበር ታሪኩን ያወሱት። «. . . በሠራዊቱ መሐል አዝማሪዎችም አብረው ይዘምታሉ፡፡ በዚያ ሁሉ ሁካታ አዝማሪዎቹ ዘማቹን እያጫወቱ ይሄዳሉ፡፡ አብሯቸው የሚጓዘው ሠራዊትም ለአዝማሪዎቹ ግጥም እየነገሩ ነበር ጉዟቸውን አብረው የሚያደርጉት፡፡ አዝማሪዎቹ የደከመውን በግጥም እያበረታቱ ይጓዛሉ» ይላሉ። ለአብነት
«ወንድሜ ራበህ ወይወንድሜ ጠማህ ወይ
አዎን የናቴ ልጅ እርቦህ ጠምቶሃል
ታዲያ የናቴ ልጅ አዳኝ ወፍ አይደለህም ወይ?
ግፋ ብረር ወደፊትህ ሂደህ ጠላትህን አትበላም ወይ?
ግፋ ወደፊት ከበዓሉ ቦታ ፈጥነህ ድረስ
የምታርደውን ሥጋ የማቆራርጥልህ እኔ ነኝ
ግፋ የናቴ ልጅ ውሃ ጠምቶሃል
ጠጅ ብታጣ ደሜን እንድትጠጣ እሰጥሃለሁ» እያሉ ግጥም ይደረድራሉ።

ከአዝማሪዎች ተርታ
አሁን ደግሞ ወደ አዝማሪዎችና ሌሎች ያልታወቁ ገጣሚዎች የተቀኟቸው ቅኔዎችና ዜማዎች አለፍን። እነዚህ ቅኔዎች በድግስ ላይም ይሁን በመሸታ መጠጥ ቤት ንጉሦችና አርበኞች የተወደሱበት ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ
«እስኪ ለጣሊያኖች መድኃኒት ስጧቸው
የሚያስቀምጥ ሳይሆን የሚያስመልሳቸው።» የሚለውን ብናይ በመሸታ ቤት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ቅኔዎች ሲዘረፉ እንደ አውዱ ስለሚሆን ነው። የቅኔው ሰም መድኃኒት ሲጠጣ ቁልቁል የሚል እንዳለ ሁሉ የሚያስመልስም ይኖራል እና ለጣሊያኖች የሚያስመልሰው ይሁን ነው። ዋናው መልዕክት ግን ያለው ወርቁ ላይ ነው። ጣሊያን ኢትዮጵያ ውስጥ መቀመጥ የለበትምና በመጣ እግሩ ወደ ሀገሩ ይመለስ ለማለት ተፈልጎ ነው ይህ የተባለው።
ጣሊያን ለቅኝ ግዛት ሲመጣ እንደ ኢትዮጵያ ኋላ ቀር መሣሪያ ሳይሆን ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ ነበርና  በመሣሪያ ብዛትና ዘመናዊነት ሳይሆን በወኔና በስልት መዋጋት ሲቻል ነው ድል የሚመጣው ለማለት እንዲህ ተብሏል።

«በሠራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ
ተፈፀመ ጣሊያን አበሻ እንዳይደርስ።»

ጣሊያን ይህ ሁሉ ሽንፈት ሲደርስበት የሮም ሴቶች ጀግና አይወልዱም ለማለት ደግሞ እንዲህ ተብሏል።

«መካኖቹ ብዙ በሮም በሶሪያ
ወላድ እጅጋየሁ በኢትዮጵያ።»

መምከርና ማስተማር ቢቻልም ጠላት ግን ያው ጠላት መሆኑን ለመንገርም እንዲህ በማለት ተገጥሟል።

«ይመከራል፣ ወይ ይማራል፣ ይረዳል ብዬ እንጂ
ወትሮስ ምን ሊሆነኝ የጥላት ወዳጅ
በል አትናድብኝ አትሸበር ሆዴ
ጥንቱን ይመልሳል የአባትህ ጎራዴ
ጎበዝ መርዝ በል አልመህ ምታ
ሳያልቅ እንዲጨርስ ያጎረስከው ካርታ»
የአባቶች አደራን ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማውሳት ደግሞ እንዲህ ነበር  ተብሎ የተገጠመው።
«እንግዲህ ሸለቆው ቋጥኙም ይደማል
በማንጊዜ ጠላት አገርን ያስማማል
አትነካኩኝ አትግፉኝ አልኩ'ንጂ
ምን አንቅልባስ አለኝ የጠላት ወዳጂ
ጎበዝ ክተት አትስማ ከልካይ
የአባትህ አደራ ይከብዳል ከድንጋይ።
ቆራጥነታቸውን ሲናገሩ ደግሞ  
እንግዲህ አይኖርም ነገር ማለሳለስ
እነርሱም አያርፉ እኔም አልመለስ
የክፉን ሰው ዋሻ ምን አለም ይሏታል 
ከሀዲ ሲከዳት ጎበዝ ይነዳታል።» 


ከዚያ ደግሞ እረኛው ባለቅኔ በግጥሞቹ እንዲህ ሲል ነበር የገለጸው።
«ኧረ ጉዱ በዛ ኧረ ጉዱ በዛ
 በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ» 

ለጦር አዝማቾችም ማንቂያ ይሆን ዘንድ እንዲህ ሲሉ ይገጥሙ እንደነበር ይነገራል።

«ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ
አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ፡፡
እነዚያ ጣሊያኖች ሙግት አይገባቸው
አሉላ አነጣጥረህ ቶሎ አወራርዳቸው፡፡
ዳኛው ወዴት ሄዷል እስኪ ወጥተህ እይ
አክሱም መንገሻዬ እስኪያዝ ነወይ፡፡
ዓድዋ ላይ ጣሊያኖች የዘፈኑለት
ምኒልክ ጎራዴህ ወረደ ባንገት፡፡»

በቤተእምነቶች

የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ትውፊት መሠረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀን ስለነበርና ምኒልክም የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት ይዘውም ስለዘመቱ ለዚህም የተዜመ ዜማ እንዳለ ይነገራል። ይኸውም

«የዓድዋ አርበኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከምኒልክ ጋር አብሮ ሲቀድስ፤
ምኒልክ በጦሩ ጊዮርጊስ በፈረሱ
ጣልያንን ድል አደረጉ ደም እያፈሰሱ» እየተባለ እስከአሁን የሚዘመረው ነው፡፡

ያልጠቀስናቸው ሴቶች፣ እረኞችና ሌሎችም አሉ፡፡ ይሁንና ከላይ እንዳልናቸሁ ሁሉንም መዘርዘር ያዳግታል፡፡ ስለዚህ በዚህ ይብቃን፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር እየተባለ በዓለም የታሪክ ድርሳናት የሚወሳው በጀግኖች ደምና አጥንት ነው። ዓድዋ ያለፈ ታሪክ ነው ብለን የምንተወው ሳይሆን ዛሬም ነገም የምንኮራበት ህያው ታሪካችን ነውና በጉዳዩ ላይ ሁል ጊዜ ማውጋት እንችላለን። ስለዚህም ክብር ለደሙ ለቆሰሉና በክብር ህይወታቸውን ለሰዉ ሰማዕታት፣ ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን፣ ክብር ለኢትዮጵያዊያን ይሁን እያልን ጽሑፋችንን እንቋጭ።



ጽጌረዳ ጫንያለው



2 comments:

  1. https://www.youtube.com/watch?v=R-w-JIoBTn4

    ReplyDelete
  2. https://www.youtube.com/watch?v=Mp7gdmhOiWY
    eshome Asegid - ዘራፌዋ (Zerafewa) - 1981 E.C.

    ReplyDelete