የጥናት ስምምነት
ኢትዮጵያና ጃፓን ለመጀመሪያ ጊዜ
የአጋርነት እና
የንግድ ውልን በመፈራረም ግንኙነታቸውን የጀመሩት በ1922 ዓ.ም (1930 እ.ኤ.አ) ነበር:: ሁለቱ አገራት ይህን ስምምነት በተፈራረሙ በዓመቱ በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩት ህሩይ ወልደ ስላሴ ጃፓንን ለመጐብኘት ሄዱ:: በዚህ ጉብኝት ወቅትም የአገሪቱን ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ አጋርነት የሚያሸጋግር ሌላ ስምምነት ተፈራረሙ::
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሯ እና ጃፓን ደግሞ ከኢትዮጵያ ጐን ባለመቆሟ ብሎም ሁለተኛው የአለም ጦርነት ሲጀምር ጃፓን ከነጣሊያን ጋር በማበሯ ተቋረጠ:: ከ20 ዓመታት በኋላም ማለትም በ1947 ዓ.ም አካባቢ የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአዲስ ተጀመረ:: ግንኙነቱ እየተጠናከረ ሄዶም ከሶስት አመታት በኋላ አምባሳደሮችን በየአገሪቱ ሾሙ::
ይህ የሁለቱ አገራት የአጋርነት እና ትብብር ስምምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መሄዱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተለያዩ ግዛቶች የመልክአምድር ጥናት ለማድረግ የሚያስችሉ ስምምነቶች ላይ ሊደረሱ ችለዋል:: ታዲያ በተመሳሳይ በወለጋ ጠቅላይ ግዛት የመልክአምድር ጥናት እንዲደረግ በኢትዮጵያ እና በጃፓን መንግሥታት መካከል ስምምነት የተፈረመው በዚህ በያዝነው ሳምንት የካቲት 29 ቀን 1965 ዓ.ም ነበር::
የጋዜጠኞች መባረር
በኢትዮጵያ የነበረው ዘውዳዊ አገዛዝ ህብረተሠቡን እኩል የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚ ካለማድረጉም ባሻገር በአገሪቱ ጭቆና እንዲንሰራፋ በማድረጉ የብሶት ድምፆች መሰማት ጀመሩ:: እነዚህ የብሶት ድምፆች በገበሬዎች፣ በወታደሮች፣ በምሁራንና በተማሪዎች በኩል በየጊዜው የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሱ ማሰማት ጀመሩ:: በተለይ ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የብሶት ድምፆች እየተጠናከሩ እና እየተባባሱ መጡ::
የብሶት ጥያቄዎቹ እየተባባሱ ቢሄዱም ከዘውዳዊው አገዛዝ አራማጆች በኩል ግን ይህን ብሶት የሚያረግብ ምላሽ ሊገኝ አልቻለም:: በተለያዩ አካባቢዎችም የተማሪዎች እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ቀጠሉ::
ታዲያ ለእነዚህ የተማሪዎች እንቅስቃሴዎች የገንዘብ እርዳታ አድርገዋል በሚል በኢትዮጵያ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሶስት የሩሲያ ጋዜጠኞች እና ሶስት የቼኮዝሎቫኪያ ዲፕሎማቶች ከአገሪቱ እንዲባረሩ የተደረገው በዚህ በያዝነው ሳምንት መጋቢት ሁለት ቀን 1961 ዓ.ም ነበር::
ምንጭ ፤ በኩር የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment