Wednesday, March 7, 2018

ዳግም ታሪክ-በዳግማዊ


ዳግም ታሪክ-በዳግማዊ




በመላው የዓለም ክፍል የሚገኙ ሰዎች ከአለት ድንጋይ ተፈልፍለው የታነፁ የጥበብ አሻራዎችን ማድነቅ ከፈለጉ ምርጫቸው አንድ ብቻ ነው፤ የጉዞ መስመራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ማድረግ:: ነገሩን ጠበብ ለማድረግ ያህል ብቸኛው የጉብኝት መዳረሻ የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ይሆናሉ::

ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት በቅዱስ ላልይበላ የማይሞከር ከሚመስለው አለት ተፈልፍለው የተቸሩን የጥበብ አሻራዎቻችን ግን በአንዳንድ ተጠራጣሪዎች ዘንድ፣እውን በኢትዮጵያውያን የታነፁ ናቸውን? የሚል የጥርጣሬ ጥያቄን እንዲያነሱ አድርጓል፣፣ ምክንያታቸው ደግሞ እኒያ የላልይበላ ፍልፍል አብያት ክርስቲያናትን ያነፁ እጆች፣ የፋሲል አብያተ መንግስታት ህንፃዎችን የገነቡ እጆች ዛሬ የት ደረሱ? የሚል ነው::
እነዚህን የጥበብ አሻራዎቻችን እኛው በእኛው የታነፁና የተገነቡ መሆናቸውን እምነት ያሳደሩ ደግሞ በበኩላቸውእናንተ ኢትዮጵያውያን የኋሊት እየተጓዛችሁ ነው!” ሲሉ ተሳልቀውብናል:: ለዚህም ደግሞ ላልይበላን ያነፁ የጥበብ እጆች አሁን ላይ መጠበብን እንዴትስ ተሳናቸው! የሚለው ተመሳሳይ ምክንያት ነው::

እነዚህን ውስን አብነቶች ማንሳታችንም ለአብነቶቹ መነሻ ምክንያት መሆን መንስኤ ወደ ሆነው ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን በድፍረት ለመንደርደር ያስችለናል::

የኋሊት ጉዟችንን አስቀርቶ አዲስ ብስራትን ያበሰረን ጥበብ ብቅ ያለው የቅዱስ ላልይበላ የጥበብ አሻራዎች ከሚገኙበት አካባቢ የተጎራበተ ነው:: “ዳግማዊ ላልይበላየሚል መጠሪያ የተቸረው ይሄው ኪነ ጥበብ ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ በዋድላ ወረዳ ይገኛል::

ጉዞ ወደ ዳግማዊ ላልይበላ

ከባሕር ዳር 240 ያህል ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኘው ጋሸና ከተማ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወልድያ ከተማና ሌሎች የአካባቢው ከተሞችን የሚጋናኝ የአስፋልት መንገድ አላት:: ከከተማዋ ምስራቃዊ አቅጣጫ በኩል ደግሞ 61 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የዓለም ቅርሶቹ የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ:: ነገር ግን የአስፋልት መንገድን የተራበ የጠጠር መንገድ መሆኑን ልብ ይሏል:: እኛም የጉዞ መሥመራችንን ከጋሸና ወደ ላልይበላ አቅጣጫ አድርገናል:: ወጣ ገባ የበዛበት የጉዞ መስመራችን ግን አምስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ተገድቧል፤ ምክንያቱም ወደ ዳግማዊ ላልይበላ የሚያደርሰው የመኪና ላይ ጉዞ በዚህ ርቀት ላይ ስለሚቋጭ።

ከአምስት ኪሎ ሜትር የመኪና ላይ ጉዞ በኋላ የጉዞ አቅጣጫችንን ወደ ሰሜን አድርገን የእግር ጉዟችንን ተያይዘነዋል:: በምዕራብ በኩል ከሰሜን ወደ ደቡብ የተዘረጋ በልቶ የጠገበ የሚመስል ግዙፍ ተራራ ይታያል፤ አረንጓዴ ሸማን የተጐናፀፈ የሚመስለው ይህ ቦታ ለዕይታ በእጅጉ ይማርካል:: በተፈጥሯዊው ውበት እየተደነቅን ከአስራ አምስት ደቂቃዎች የእግር ጉዞ በኋላ አፍን በአግራሞት በእጅ የሚያስይዘው ቦታ ላይ ደረስን::

አካባቢው ከቅርብ ርቀት ሆነው ሲመለከቱት የአለቱ ድንጋይ ክረምት ከበጋ ውኃ የሚሄድበት የወንዝ ላይ ነጭ አለት ይመስላል፤ ቀርበው ሲመለከቱትም እንደዚያው:: አይደለም በባህላዊ የቁፋሮ መሳሪያዎች በዘመን አመጣሹ ድማሚት እንኳን ለመፈልፈል የሚታሰብ የማይመስል አለት ነው:: ነገር ግን በውስጡ ዳግማዊ ላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን ይዟል::

ከአንድ አለት ላይ የተፈለፈሉት አብያተክርስቲያናት ከሰሜን ወደ ደቡብ የታነፁ ናቸው:: የታነፁበት ወቅትም በዚያው ቅደም ተከተል ነው:: በቁጥር አራት ሲሆኑ ሁሉም ቤተ ክርስቲያናት ደግሞ የየራሳቸው መቅደስ፣ ቅኔ ማህሌት እና ቅድስት አላቸው:: ሁሉም ቤተ መቅደሶች ውስጥ ለውስጥ ተሳስረዋል። ይህም ሁሉም ሰው የአዳም ዘር መሆኑን ለማሳየት ነው:: የሁሉንም ህንፃዎች ውጫዊና ውስጣዊ ገፅታ ተዘዋውረን ከተመለከትን በኋላ ከጥበቡ ባለቤት ጋር ቆይታ አደረግን::

መሪጌታ ገብረመስቀል ተሰማ ከሁለት ረዳቶቻቸው ጋር በመሆን የዳግማዊ ላልይበላን ፍልፍል አብያተክርስቲያናቱን እውን ያደረጉ ናቸው፤ አራቱንም ለማጠናቀቅ ሰባት ዓመታት ወስዶባቸዋል:: ከዚህ ጊዜ ውስጥ ግን ሦስቱ ዓመታት በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘታቸውና በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት የባከኑ ነበሩ:: ይህ ማለት ደግሞ ፍልፍል አብያተክርስቲያናቱ ተጀምረው ለፍፃሜ የበቁት በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ መሆኑን ልብ ይሏል::

ከልጅነቴ ጀምሮ የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት በኢትዮጵያውያን አልታነፁም ብለው ለሚጠራጠሩ ምላሽ ለመስጠትና ለማረጋገጥ ፍላጐቱ ነበረኝበማለት ሀሳቡ እንዴት እንደተጠነሰሰባቸው ነገሩን:: ከዚህ የሐሣብ ልውውጥ በኋላም ከአለት ላይ ከሰሜን ወደ ደቡብ ተፈልፍለው የታነፁትን አራቱንም አብያተ ክርስቲያናት የአሰራር ጥበብና ትርጉም በተመለከተ በሰፊው ተጨዋወትን::


የጥበቡ መጀመሪያ

በስተሰሜን በኩል የሚታየው ፍልፍል ህንፃ ክብ ሆኖ የመሶብ ቅርፅ ያለው ነው፤ ይህ መሆኑ ደግሞ የሰማያዊት ደብረ ፅዮን ተምሳሌትነትን ያሳያል፤ ክርስቶስ ዓለምን ለማሳለፍ ወደ ዚህ ዓለም ሲመጣ የሚፈርድባት የዙፋኑ ተምሳሌት መሆኗን መሪጌታ ገለፁልን:: ዙሪያው ሰላሳ ስድስት ቅርፆች አሉት፤ የሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳን ምልክቶች ናቸው። አስራ ሁለቱ በሮች ደግሞ የአስራ ሁለቱን ሐዋርያት ይወክላሉ:: የተከፈቱት ግን ሶስቱ በሮች ብቻ ናቸው:: የሶስቱ በሮች መከፈት ደግሞ የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን አንድ አምላክነትና ሦስትነት የሚያሳይ መሆኑን መሪጌታ ገብረመስቀል ነግረውናል:: ከዚህ በተጨማሪም ሀያ መስኮቶች አሉት።

የክብ ቅርፅ ያለው ይሄው የመጀመሪያው ፍልፍል ህንፃ መሶብ የመሰለ ገፅታ ያለው ሲሆን ላዩ ግን የተከፈተ አይደለም:: ይህም ድንግል ማርያም ክርስቶስን ከፀነሰችውና ከወለደችውም በኋላ ማህተመ ድንግልናዋ እንደ ነበር ለመግለፅ ተምሳሌት ተደርጐ የታነፀ ነው::

የዚህ ፍልፍል ህንፃ ረቂቅነት በዚህ ተምሳሌትነት ብቻ አያበቃም:: ከፍልፍል ህንፃው በታች በኩል 81 መቁጠሪያዎች አሉ፤ ይህም የሐዲስና የብሉያት ተምሳሌት መሆኑን ነግረውናል::

አሁን የመጀሪመያው ፍልፍል ህንፃ ጉብኝትን አጠናቀን ወደ ሁለተኛው ልዩ ጥበብ ልንሻገር ነው፤ በዚህ ወቅት ግን መሪጌታ ገብረመስቀል ሌላ አግራሞት የፈጠረብንን ሀሣብ ሰነዘሩልን:: “ይሄን ፍልፍል ህንፃ ስናንፅ መጀመሪያ ላይ ቅርፁን አናውቀውም፤ ጥበቡ ሲሰራ በእግዚአብሔር መሪነት ነው:: ሁሉም ንድፍና ሐረግ በራሱ ነው የሚገለጥልን:: እኛ የምናደርገው ከላይ ወደታች ህንፃዎቹን እየጨረስን መሄድ ብቻ ነው::በዚህም የመጀመሪያውንና የአንድ ዓመት ጊዜ የጨረሰውን ፍልፍል ህንፃ ጉብኝት በማጠናቀቅ ወደ ሁለተኛው አመራን:: አራቱም ፍልፍል ህንፃዎች እያንዳንደቸው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የታነፁ ናቸው።

ወደ ቀጣዮቹ ውብ ፍልፍል ህንፃዎች በመሻገር ያየሁትን ለመግለፅ ስስታም ሆኛለሁ፤ ለነገሩማ የትናንትናዎቹን የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ጥበብ ዛሬ ላይ ሲደገም እንዴትስ አለመሳሳት ይቻላል! ነገር ግን ዓይኔ የደስታ እንባ ያነባባቸው እነዚህን የዳግማዊ ላልይበላ የአለት ላይ ፍልፍል አብያተክርስቲያናት ጥበብ በውስጤ አምቄ ማስቀመጥ አልተቻለኝም::

ወደ ሁለተኛው ፍልፍል ህንፃ ውስጣዊ ገፅታ ከመሸጋገራችን በፊት ግን ሀሣቤን በሚቀጥሉት ስንኞች መጀመርን ምርጫየ አድርጌያለሁ::

ኧረ እንደምን አርጐ ሰራው፣
ኧረ እንደምን አርጐ አነፀው፣
የመጥረቢያው እንኳ እጀታ የለው::
ዓይኔ ጉድ አዬ እግሬ ደርሶ፣
የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ ምሰሶ::

ከላይ ያሰፈርናቸው ስንኞች ከእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጋር ተያይዞ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሚነገሩ ናቸው፤ የልደት በዓል ሲነሳ ደግሞ የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን አለማንሳት የማይታሰብ እውነታ ነው:: የቀሳውስቱን የቤዛ ኩሉ ሥርዓትን አለማስታወስና በመንፈሳዊ የደስታ ባህር ውስጥ አለመዋኘትስ እንዴት ይቻላል! የስንኞቹ መቋጠር ደግሞ የነዚህን ዘመን ተሻጋሪ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት እፁብነት አጉልቶ ለማሳየት ነው::

ይሁን እንጅ እዚህ ላይ ስንኞቹን ማንሳታችን ስለነዚህ የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት የምንላችሁ ሀሣብ ኖሮን አይደለም:: ምናልባትም የስንኞቹን መልዕክት በሁለተኛነት የሚያጣጥምና የሚዘመርለትን ዳግማዊ ላልይበላን ለማስቃኘት እንጅ::

ሁለተኛው ጥበብ

ይህ ፍልፍል ህንፃ በምስራቅ በኩል ውጭ ላይ ሆነው ሲመለከቱት በትልቅ መስቀል ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ካርታ /ኤርትራን ያካተተ/ በጉልህ ይታያል፤ ከካርታው ላይ ደግሞ በመጠን አነስ ያለ ሌላ መስቀል አርፎበታል:: ምስጢራዊነቱ አልገለጥልን ቢለን አሁንም መሪጌታ ገብረመስቀልን እንዲያብራሩልን ጠየቅናቸው::

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች! ብሎ ነብዩ ቅዱስ ዳዊት በብቸኝነት የጠቀሳት ኢትዮጵያን ነው፤ ይህም ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በመስቀሉ ተጠብቃ እንደምትኖርና መንበር በመሆንም መላውን የዓለም ሀገራት በመስቀሉ እንደምትጠብቅ ያሳያል!” አሉን::

ከዚሁ ፍልፍል ህንፃ ውስጥ ዘልቀው ሲገቡ አራት ዋና እና አንድ ለየት ያለ በሮች ይታያሉ፤ ሁሉም በሮች የመስቀል ቅርፅ ተቀርፆባቸዋል:: ለየት ያለው በር በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ክርስቶስ ስጋ ለብሶ ከድንግል ማርያም ሲወለድ ዙፋኑን ያመለክታል:: አራቱ በሮች ደግሞ በወንጌላውያኑ ዮሐንስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ማቴዎስ ይወከላሉ::

ከዚህ በተጨማሪም ከላይ በኩል ቤተ አብርሐም በሚል የተቀረፀ ልዩ ጥበብም ይታያል።ደጉ አብርሐም የተራቡትንና የተጠሙትን ለማብላትና ለማጠጣት ቤቱን ከመስቀለኛ ጐዳና ላይ ነበር ሠርቶ ይኖር የነበረውአሉን መሪጌታ ገብረመስቀል::

በምስጢር የተሞላው ፍልፍል አብያተክርስቲያናት ሌሎች ብዙ ምስጢራዊ ትርጉሞችንም በውስጡ ይዟል፤ መሪጌታ ገብረመስቀል ግን መፅሐፍ እንደሚያነብ ሰው ያህል ነው ብትንትን አድርገው ምስጢራቱን የሚተነትኗቸው::

ቤተ አብርሐም በሚል ተቀርፆ ምስል ካረፈበት መስቀለኛው ቦታ በኩል ዕይታዎን ሲያሳልፉ ደግሞ ስድስት ጋኖች ተቀርፀው በስርዓት ተደርድረው ይታያሉ፤ እነዚህም በቃና ዘገሊላ ዕለት ክርስቶስ በሰርግ ቤት በተገኘበት ወቅት ሰርገኞች ወይን ሲያልቅባቸው ውኃውን ወደ ወይን የቀየረበትን ምስጢር የሚገልፁ ናቸው:: በዚሁ በኩል ጉዞዎትን ሲቀጥሉም ከበሩ በላይ በኩል የሐዲስ ሕግ /ሕገ ወንጌል/ እና በታች በኩል የብሉይ ሕግ /ሕገ ኦሪት/ ይታያሉ፤ ላይና ታች መቀመጣቸው ደግሞ የሕገ ኦሪት ፍፃሜ ሕገ ወንጌል መሆኗን ለማመልከት እንደሆነ መሪጌታ ገብረመስቀል ነግረውናል::

ሶስተኛው ጥበብ

ከላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት መካከል ቤተ ጊዮርጊስ በቤዛ ኩሉ ሥርዓት ይበልጥ በየዓመቱ ይደምቃል፤ የመላው ዓለም ጐብኝዎችን ቀልብም ይስባል:: አሁን እያስቃኘናችሁ የምንገኘው የዳግማዊ ላልይበላ ፍልፍል አብያተክርስቲያናት በተለይ ሦስተኛው ፍልፍል ህንፃ ደግሞ ከቤተ ጊዮርጊስ ጋር የሚመሳሰል ነው:: ከላይ ሲመለከቱት የሦስት መዓዘን ቅርፅ ያለው ነው:: ይህ መሆኑ ደግሞየአብ፣ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስን ሦስትነትና አንድነት ለመግለፅ ነው::” ብለውናል መሪጌታ ገብረመስቀል::
ወደዚሁ ፍልፍል ህንፃ ውስጥ ሲዘልቁ በስድት ጠርዞች ዙሪያ አስራ ሁለት ቅርፆች ይታያሉ:: ስድስቱ ጠርዞች ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ይወክላሉ፤ ከላይ የሚታዩት ቅርፆች ደግሞ የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ውክል ናቸው:: በአጠቃላይ ግን ከላልይበላው ቤተ ጊዮርጊስ ጋር በአጅጉ እንደሚመሳሰል የተነገረለት ይሄው ፍልፍል ህንፃ 12 ክንድ ርዝመት አለው:: ርዝመቱን በክንድ መግለፃችን የሁሉም ፍልፍል ህንፃዎች ርዝመትና ስፋት እየተለካ የታነፀው በክንድ ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል::

አራተኛው ጥበብ

ይህ ፍልፍል ህንፃ ከሌሎቹ ህንፃዎች በስፋቱ ይጠባል:: “የብርሃን መስጫ ነው!” በማለትም መሪጌታ ገብረመስቀል የፍልፍል ህንፃውን አብይ ተግባር ነገሩን:: ከዚሁ ፍልፍል ህንፃ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ደግሞ የአራተኛው ፍልፍል ህንፃ የተጠናቀቀበት በጅምር የቀረ አለት ይታይል:: ይህ ምልክትም ለቀጣይ የሚፈለፈሉት መሰል ህንፃዎች በዚያው በኩል መሆናቸውን ለመጠቆም ነው:: ምክንያቱም በሚቀጥሉት ጊዜያት ሌሎች ተጨማሪ ስድስት ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ስለሚታነፁ ነው::

ማጠቃለያ

የዳግማዊ ላልይበላ ፍልፍል አብያተክርስቲያናት ከአለቱ አናት ላይ ወደታች በመፈልፈል የአንዱን ህንፃ መጠናቀቅ ተክትሎ ወደ ቀጣዩ በመሸጋገር የታነፁ ልዩ ጥበብ ያረፈባቸው ናቸው:: አንድ ወጥ አለትን ፈልፍሎ ሲጀመርም ምን ዓይነት ህንፃ እንደሚታነፅ አንኳን ቀድሞ በውል አይታወቅም::

አብያተክርስቲያናቱ የተሠሩት እንደ መሐንዲሶች በወረቀት ንድፍ ተሠርቶ ሳይሆን በክንድ እየተለካ ነው:: ህንፃዎቹ ሲፈለፈሉ ደግሞ ከባህላዊ የርዝመት መሳሪያ እና የመቆፈሪያ ቁሶች ውጭ ሌላ ነገር አልተጠቀሙም:: ተፈልፍሎ የሚወጣው ጠጠር እንኳን የሚጓጓዘውና የሚከማቸው ድንጋይን በመጥረብ በተዘጋጀ ባህላዊ ጋሪ /ካሬታ መሰል/ አማካኝነት ነው::

ታዲያ ይህ ሁሉ እፁብ ድንቅ ያስባለን፣ የትናንት አሻራችንን ዛሬ ላይ ነጋሪ የሆነ ሥራ በሁለት ረዳቶች በመታገዝ በመሪጌታ ገብረ መስቀል ነው የተበረከተልን::

የጉብኝት ሁኔታ

ዳግማዊ ላልይበላ በአራት ዓመታት ውስጥ ሥራው ተጠናቆ ጥር 17 ቀን 2010 . ለምረቃ በቃ:: በዕለቱም በመጀመሪያው ፍልፍል ህንፃ በክብ ቅርፅ ሆኖ በድንግል ማርያም ተምሳሌት የተደረገው ቤተክርስቲያን በሰሜን ወሎ ሀገር ስብከት ረዳት ሊቃነ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ኤርሚያስ ቡራኬ ተደርጐ የማርያም ፅላት ወደ መንበሯ ገብታለች:: በርካታ ምዕመናንም ዕድምተኞች ሆነው ነበር::

መሪጌታ ገብረመስቀል የዓመታት ሥራቸው እውን በመሆኑ ደስታቸውን ገልፀው የአሁኑ ትውልድም በመልካም ተግባር የአባቶቹን አደራ እንዲያስቀጥል አደራ ብለዋል::

ሁሉም ጉብኝት የሚካሄደው የኢትዮጰያን ባህልና ወግ በጠበቀ መልኩ እንደሆነም መሪጌታ ተናግረዋል:: የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ጐብኝዎች ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱን ለመጐብኝት ሲመጡ ባህላዊ ቀሚስና ጋቢ እንዲለብሱ ይደረጋል፤ አስተናጋጆች /አስጐብኝዎች/ ደግሞ በርኖስ፣ ዳባ እና ሌጦ ልብስ በማዘጋጀት እንዲለብሱ ይደረጋል::

በኩር ጋዜጣ የካቲት 26/2010 / ዕትም

No comments:

Post a Comment